አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ስምንት የሳድ ስርዓቶችን ታንቀሳቅሳለች።
ዋሽንግተን ፖስት እና የደቡብ ኮሪያ የዜና ምንጮች ባለስልጣናትን ጠቅሰው እንደዘገቡት፤ አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ የተተከለውን የሚሳዔል መከላከያ ስርዓት ከፊል አካላትን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያዛወረች ነው።
ይህ እርምጃ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት በጀመሩ በ12ኛው ቀን የመጣ ሲሆን፤ ይህም ኢራን በጆርዳን የሚገኘውን የሳድ ሲስተም ቁልፍ ራዳር ማውደሟን የሚጠቁሙ ዘገባዎችን ተከትሎ ነው።
ሳድ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ኮሪያ የሰፈረው በ2017 ኒውክሌር ከታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ የሚመጣን ስጋት ለመከላከል ነበር።
ድርጊቱ ትልቅ ኢላማ ያደርገናል ብለው በሰጉ ደቡብ ኮሪያውያን ዘንድ ቁጣንና ተቃውሞን ያስከተለ ሲሆን፤ቻይና በበኩሏ ቀጣናውን ሊያናጋ ይችላል ስትል አስጠንቅቃለች።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዋሽንግተን ፖስት ሁለት ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የሳድ ሲስተም ክፍሎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እየተጓጓዙ ነው።
ዘገባዎቹ የወጡት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ባሉበት እና ኢራን በበኩሏ በቀጣናው የሚገኙ የእስራኤል እና የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በባሊስቲክ ሚሳዔሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየመታች ባለችበት ወቅት ነው።
ኢራን በትክክል ምን ያህል ሚሳዔሎች እንዳሏት ግልጽ ባይሆንም፤ ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው እስካሁን ከ500 በላይ የባሊስቲክ ሚሳዔሎችን ተኩሳለች።
አብዛኛዎቹ ሚሳዔሎች ቢመከቱም የሚመጣው ተኩስ ብዛት የዋሽንግተንን ወታደራዊ ክምችት ሊያሟጥጥ ይችላል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በተጨማሪም ኢራን የአሜሪካን አጋሮችን ጨምሮ አብዛኛውን መካከለኛው ምስራቅን ለሚያካትት የረጅም ጊዜ ጦርነት ራሷን እያዘጋጀች ነው ተብሎ ስለሚታመን ጥቃቱ ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል።
የደቡብ ኮሪያ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ የሳድ ሚሳዔል መተኮሻዎች ከሴኦንግጁ አየር ኃይል ጣቢያ እየወጡ ነው።
ፕሬዝዳንት ሊ ጄምዩንግ ሴኡል የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች እንዳይወጡ መቃወሟን ገልጸዋል፡፡
ተቃውሟችንን ብንገልጽም እውነታው ግን አቋማችንን ሙሉ በሙሉ ማስፈጸም አንችልም ሲሉም አክለዋል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 04/2018 ዓ.ም
