በአምስት ዓመቱ የውድድር መኪና አሽከርካሪነት ፈቃድ ያገኘው ቻይናዊ ታዳጊ

​በዓለም ላይ ትንሹ ብቁ የውድድር መኪና አሽከርካሪ በመሆን የሚታወቀው ቻይናዊው ሻኦ ዚያን፣ ገና በአምስት ዓመቱ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

አብዛኞቹ ሕፃናት ገና መራመድ በሚጀምሩበት በአንድ ዓመት ዕድሜው የመኪና መንዳት ልምምድ መሣሪያዎችን መጠቀም የጀመረው ሻኦ፣ ሦስት ዓመት ሳይሞላው የውድድር ካርቶችን መንዳት ችሏል።

በአራት ዓመቱ በቻይና የራሊ ስፕሪንት ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ “የተስፋ ኮከብ” ሽልማትን ያሸነፈ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ የዲጂታል መኪና ውድድሮችም ከምርጥ 30 አሽከርካሪዎች ተርታ መሰለፍ ችሏል።

​ልጁ ላሳየው ከፍተኛ ተሰጥኦ አባቱ ከ116 ሺህ ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የራሊ መኪናዎችንና ዘመናዊ መለማመጃዎችን ያዘጋጁለት ሲሆን፣ በውድድሮች ላይም የልጃቸው ረዳት አሽከርካሪ በመሆን ያገለግላሉ።

ሻኦ ዚያን እ.ኤ.አ. በ2023 በቻይና አውቶሞቢልና ሞተር ሳይክል ፌዴሬሽን የተረጋገጠ የብቃት ምስክር ወረቀት በመቀበል በሀገሪቱ ትንሹ ፈቃድ ያለው አሽከርካሪ ለመሆን በቅቷል።

ታዳጊው ከብዙ አዋቂዎች የተሻለ የመንዳት ብቃት ቢኖረውም፣ የሀገሪቱን የትራፊክ ደህንነት ሕግ ለማክበር ሲባል በሕዝብ መንገዶች ላይ መንዳት አይፈቀድለትም፤ በመሆኑም የውድድር መኪኖቹ ወደ ውድድር ቦታ የሚጓጓዙት በጭነት ተጎታች መኪናዎች አማካኝነት  መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።

ሐመረ ፍሬው

መጋቢት 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *