ትራምፕ የኢራን መሪዎችን በመግደላቸው ‹‹እንደሚኮሩ››ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን መሪዎችን ‹‹አዕምሯቸው የተዛባ›› በማለት ያንቋሸሹ ሲሆን፤ እነሱን መግደል ትልቅ ክብር እንደሆነ ተናግረዋል።

በእስራኤል እና በአሜሪካ የጋራ ጥቃት በኢራን ላይ የተጀመረው ይህ ግጭት ከ2 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለ፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ያመሰቃቀለ እና በዓለም ዙሪያ የኢነርጂ እና የፋይናንስ ገበያዎችን ያናወጠ ነው።

ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልእክት አሜሪካ የኢራንን አሸባሪ አገዛዝ ‹‹ሙሉ በሙሉ›› እያወደመች ነው ብለዋል።

እኛ አቻ የማይገኝለት ኃይል፣ ገደብ የሌለው የጦር መሳሪያ እና በቂ ጊዜ አለን፤ ዛሬ በእነዚህ ብልሹዎች ላይ የሚደርሰውን ትመለከታላችሁ ሲሉ ቀጣይ ጥቃቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ለ47 ዓመታት በመላው ዓለም ንጹሃን ዜጎችን ሲገድሉ ቆይተዋል፤ አሁን ደግሞ እኔ የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዝዳንት ሆኜ እየገደልኳቸው ነው። ይህን ማድረግ ምንኛ ታላቅ ክብር ነው! ሲሉ ገልጸዋል።

አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ካሜኒ በሰጡት የመጀመሪያ አስተያየት፤ቁልፍ የኢነርጂ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደተዘጋ እንዲቆይ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

ጎረቤት ሀገራት በግዛታቸው ያሉትን የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እንዲዘጉ፣ ካልሆነ ግን በኢራን ኢላማ የመሆን አደጋ እንደሚጋረጥባቸው አስጠንቅቀዋል።

አስተያየታቸው በቴሌቪዥን አቅራቢ የተነበበ ሲሆን፤ በአካል ያልቀረቡበት ምክንያት ግልጽ አልነበረም።

የኢራን ባለስልጣናት መሪው ቀላል መቁሰል እንደደረሰባቸዉ ሲናገሩ፤ትራምፕ ግን በህይወት ቢኖሩም ‹‹ተጎድተዋል›› ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ሊዲያ ደሳለኝ

መጋቢት 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *