በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ያለው የእንቅስቃሴ መቋረጥ የብሬንት ድፍድፍ ዘይት በአንድ በርሜል ከ106 ዶላር በላይ እንዲሆን አድርጓል፡፡
ለዓለም አቀፍ ዋጋዎች በጣም አስፈላጊው መለኪያ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ዘይት፤ ትናንት እስከ 3 በመቶ በማደግ በአንድ በርሜል ከ106 ዶላር በላይ የደረሰ ሲሆን፤ ዛሬ ማለዳ ላይ ደግሞ በትንሹ ቀንሶ በ104.63 ዶላር ላይ ይገኛል።
የቅርብ ጊዜው የዋጋ ጭማሪ የመጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሌሎች ሀገራት ዋሽንግተን ከዓለም የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛ የሚጓጓዝበትን የባህር ወሽመጥ እንድትከፍት እንዲረዷት ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነው።
የትራምፕ ሀሳብ እስካሁን ድረስ ቀዝቀዝ ያለ ምላሽ ያገኘ ሲሆን፤ በስም የጠቀሷቸው ቻይና፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች አገራት የባህር ወሽመጡን ለመጠበቅ የባህር ኃይላቸውን ለማሰማራት እስካሁን በይፋ ቃል የገቡ የሉም።
ትራምፕ ከፋይናንሺያል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ለቀረበላቸው ሀሳብ ምንም ምላሽ ካልተገኘ ወይም ምላሹ አሉታዊ ከሆነ ኔቶ በጣም መጥፎ የወደፊት ጊዜ እንደሚገጥመው ተናግረዋል።
ጃፓን እና አውስትራሊያ ዛሬ ማለዳ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን የመላክ ዕቅድ እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ኢራን በአገሪቱ ላይ ለተፈጸመው የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ ያለውን የመርከብ እንቅስቃሴ እንዲቆም ያደረገች ሲሆን፤ ይህም ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ በታሪክ ውስጥ ከፍተኛው የዓለም የኃይል አቅርቦት መስተጓጎል ሲል የገለጸውን ሁኔታ አስከትሏል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከ40 በመቶ በላይ የጨመረ ሲሆን፤ይህም የነዳጅ ዋጋን በመጨመር በዓለም ኢኮኖሚ ላይ መቀዛቀዝ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም የባህር ንግድ ኦፕሬሽን ማዕከል መረጃ ከሆነ፤ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቀን በአማካይ ከሚጓዙት 1መቶ38 መርከቦች በተቃራኒ አሁን በየቀኑ ከአምስት የማይበልጡ መርከቦች ብቻ በወሽመጡ በኩል ያልፋሉ።
ጦርነቱ በየካቲት 28 ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ 16 የንግድ መርከቦች በክልሉ ጥቃት እንደደረሰባቸው ድርጅቱ አስታውቋል።
ትራምፕ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በኢራን፣ በኦማን እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚዋሰነው የባህር ወሽመጥ በኩል የንግድ መርከቦችን ለማጀብ የአሜሪካን ባህር ኃይል ለማሰማራት ፍቃደኛ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 07/2018 ዓ.ም
