ባለሥልጣናት እንደገለጹት በማዕከሉ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ሕክምና እየተከታተሉ ነበር።
የታሊባን መንግሥት ፓኪስታንን ተጠያቂ ባደረገበትና በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ በሚገኝ የአደንዛዥ ዕፅ ሕክምና ማዕከል ላይ በተሰነዘረ የአየር ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸዉ አልፏል አልያም ቆስለዋል፡፡
በካቡል የሚገኘው ማዕከል ሰኞ ምሽት ላይ መመታቱንና ጥቃቱም የሰዎችን ሕይወት መቅጠፉንና ሌሎችን ማቁሰሉን የመንግሥት ቃል አቀባይ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
ፓኪስታን ማንኛውንም የጤና ተቋም መምታቷን ያስተባበለች ሲሆን፤ በምትኩ በካቡል እና በምሥራቃዊቷ ናንጋሃር ግዛት ወታደራዊ ተቋማትን እና የአሸባሪዎችን የድጋፍ መሠረተ ልማቶችን በዒላማነት መምታቷን ገልጻለች።
ቢቢሲ አሁንም በከፊል በእሳት እየተቃጠለ ያለውን ማዕከል ጎብኝቶ፤ ከ30 በላይ አስከሬኖች በቃሬዛ ተጭነው ሲወጡ መመልከቱን ዘግቧል፡፡
እንደ ማዕከሉ ባለሥልጣናት ገለጻ፤ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ይታከሙ የነበረ ሲሆን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሎ ይታመናል።
የአፍጋኒስታን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሻራፋት ዘማን ፤ ለመልሶ ማቋቋሚያ ማዕከሉ ቅርብ የሆነ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ተቋም እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የታሊባን መንግሥት ቃል አቀባይ የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 400 መድረሱን ቢናገሩም፤ ቢቢሲ ግን ይህን ቁጥር በተናጥል አላረጋገጠም።
የፓኪስታን የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ጥቃቶቹ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄና በዒላማ የተፈጸሙ ናቸው ብሏል።
ቀደም ሲል የአሜሪካ ጦር ሠፈር የነበረውና ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ፤ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች በብዛት የሚሰባሰቡበት ቦታ ነበር።
ታሊባን በነሐሴ 2021 ወደ ሥልጣን ሲመለስ ቦታውን ወደ አደንዛዥ ዕፅ ማገገሚያ ማዕከልነት በመለወጥ፣ ከዋና ከተማዋ የተሰበሰቡ ሱሰኞችን እዚያ እንዲቆዩ አድርጓል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 08/2018 ዓ.ም
