ኢሶዴፓ ወጣቶች በፖለቲካው ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ወጣቶች ከምርጫና ከፖለቲካዊ ሂደቶች ራሳቸውን ከማግለል ተቆጥበው፣ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።

ፓርቲው በአሁኑ ወቅት ወጣቱን የሚፈትኑ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ቢኖሩም፣ ከፖለቲካው መራቅ ግን መፍትሔ እንደማይሆን አመልክቷል።

ይልቁንም ራስን ማግለል በወጣቶች ሕይወት ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ያለፍላጎታቸው እንዲቀጥሉ ያደርጋል ብሏል።

ስለሆነም ወጣቶች ለምርጫ በመመዝገብና የመራጭነት ካርዳቸውን በመውሰድ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

የኢሶዴፓ ሊቀ-መንበር ዶክተር ራሔል ባፌ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ወጣቶች ባለፉት ስድሳ ዓመታት ለፍትህና ለነፃነት የተከፈለውን መስዋዕትነት ከግብ ለማድረስ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሊቀ-መንበሯ አክለውም፣ ኢትዮጵያ በሕዝብ ስልጣን ላይ የተመሰረተ መንግስት እንዲኖራት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ትግል ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ወጣቶች ይህንን የትግል ታሪክ እንደ መሠረት በመጠቀም፣ በቀደመው ትውልድ ትከሻ ላይ ቆመው ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለዚህም ለሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ካርድ በመውሰድ መዘጋጀት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎች በጥልቀት መመርመር እንዲሁም ለሀገርና ለወጣቱ የሚበጀውን ለይቶ ማወቅ እንደሚገባ ዶክተር ራሔል አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ትውልድ ለሥራ አጥነት፣ ለትምህርት ጥራት መጓደልና ለስደት መጋለጡን የገለጹት ሊቀ-መንበሯ፤ በተለይም በግጭቶችና በጦርነቶች ግንባር ቀደም ሰለባ እየሆነ ያለው ይኸው የህብረተሰብ ክፍል መሆኑን ጠቁመዋል።

“ይህ ችግር እንዲቆም ወጣቶች ወደ ሰላም የሚያመራውን መንገድ በቁርጠኝነት ሊያስቡበት ይገባል” ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

አዲስአለም አበበ

መጋቢት 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *