በቅርብ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢራን እና በአሜሪካ/እስራኤል መካከል ያለው ውጥረት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣናን ወደ “የውሃ ጦርነት” (Water War) ሊያስገባ የሚችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) ባለስልጣን አስጠንቅቀዋል።
በተመድ የሳይንስ ሊቅ እና ባለስልጣን ካቬህ ማዳኒ እንደገለጹት፣ ኢራን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በባህረ ሰላጤው አገራት በሚገኙ የጨው ውሃ ማጣሪያ (Desalination plants) እና የኢነርጂ ተቋማት ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች ነው። ይህ ድርጊት ቀጣናውን ወደ ከፋ የውሃ ቀውስ ሊከተው እንደሚችል አስታውቀዋል።
ይህ አዲስ ውጥረት የተቀሰቀሰው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን በ48 ሰዓታት ውስጥ የሆርሙዝ ሰርጥን ለንግድ መርከቦች ክፍት ካላደረገች፣ የኢራንን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች “ደመሰሳለሁ” ብለው ካስፈራሩ በኋላ ነው።
ኢራን ለትራምፕ ማስጠንቀቂያ በሰጠችው ምላሽ፦የኤሌክትሪክ ማመንጫዎቿ ከተጠቁ፣ በምላሹ በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ እና የአጋሮቿን የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ የኢነርጂ ተቋማት እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር ዝታለች።
የኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ መሀመድ ባቄር ቃሊባፍ፣ ጥቃቱ ከተፈጸመ የአካባቢው መሰረተ ልማቶች “ሊጠገን በማይችል መልኩ ይወድማሉ” ብለዋል።
ካቬህ ማዳኒ እንዳሉት በዚህ ምክንያት ሊከተል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዱ የመጠጥ ውሃ እጥረት ነው ፦ እንደ ባህሬን፣ ኳታር እና ኩዌት ያሉ አገራት ለመጠጥ ውሃቸው ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል በእነዚህ ማጣሪያዎች ላይ ጥገኞች በመሆናቸው፣ ጥቃቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከፍተኛ ጥም እና ስደት ሊዳርግ ይችላል።
ሌላው አለማችን የምትጋፈጠው እውነታ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲሆን ፦ የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት እና በነዳጅ ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የዓለምን የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ በእጅጉ ሊያንሩት ይችላሉ።
እንደ ካቬህ ማዳኒ ማብራሪያ የአካባቢ ብክለት አለምን የሚያስጋ ሌላው አደጋ ነው ፦ ቀደም ሲል በኢራን የነዳጅ ማከማቻዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት “መርዛማ ጥቁር ዝናብ” (Toxic black rain) መዝነቡን የተመድ የጤና ድርጅት (WHO) አስታውቋል።
ፎክስ ኒውስ ባስነበበው ዘገባ ግጭቱ በአጠቃላይ ሲታይ ፣ ከመደበኛ ወታደራዊ ኢላማዎች ወጥቶ ወደ ሲቪል መሰረተ ልማቶች (ውሃ እና መብራት) እየተሸጋገረ መሆኑ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በእጅጉ አሳስቧል ።
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
