ስምንት የሀገር በቀል ባህላዊ መድኃኒቶችን በዘመናዊ መልክ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ተባለ

የኢትዮጵያን የባህል ህክምና እውቀት ወደ ዘመናዊ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት፤ ስምንት የተለያዩ ባህላዊ መድኃኒቶች በዘመናዊ መልክ ተዘጋጅተው ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ እየተሰራ መሆኑን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የፋርማሲዩቲካል ኢንድስትሪ ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር መሳይ ወ /ማርያም እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚገኙ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በቅርበት በመስራት እውቀታቸውን ወደ ኢንስቲትዩቱ በማምጣት ሳይንሳዊ ምርምር ይደረግባቸዋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት መድኃኒቶቹ ያላቸውን የመፈወስ አቅም፣ የአዘገጃጀት መጠን፣ ሊኖራቸው የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳት እና ደህንነት በላቦራቶሪ እና በክሊኒካል ሙከራዎች የማረጋገጥ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በዚህ ሂደት ያለፉ ስምንት የሚጠጉ ባህላዊ መድኃኒቶች በምርምር ደረጃ ብቃታቸው ተረጋግጦ ወደ ተጨባጭ ምርት የተቀየሩ ሲሆን፤አሁን ላይ ቀጣዩ እርምጃ እነዚህን ውጤቶች ወደ የመድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች በማሸጋገር በስፋት ተመርተው የገበያ ፍቃድ በማግኘት ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ ማድረግ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

እነዚህ መድኃኒቶች የባክቴሪያ እና የፈንገስ ኢንፌክሽኖችን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች ፍቱን መሆናቸው በምርምር ተረጋግጧል ብለዋል።

ሊዲያ ደሳለኝ

መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *