በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘው የዋሊያ አይቤክስ ቁጥር በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተገለፀ

ያልተገደበ የከብቶች ግጦሽ፣ የቤት እንስሳት ተጽዕኖ እና የፓርኮች ወሰን አለመከበር ለዱር እንስሳቱ ምቹ መኖሪያ እንዳይኖር እያደረጉ ያሉ ሰው ሰራሽ ጫናዎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ፤ ምንም እንኳን የብሔራዊ ፓርኮች አጠቃላይ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፤በተለይ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘው የዋሊያ አይቤክስ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ለአካባቢያዊ ሚዛንና ለሀገሪቱ የቱሪዝም ሀብት ስጋት ሆኗል ብለዋል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም ባለስልጣኑ ዝርያ ተኮር የሆኑ የጥበቃ ስልቶችን በመንደፍና የተጎዱ የተፈጥሮ መኖሪያዎች እንዲያገግሙ በማድረግ የእንስሳቱን ቁጥርና ስርጭት ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመቆጣጠር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በአነፍናፊ ውሾች የታገዘ ፍተሻ መጀመሩንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥበቃ ስራው መጠናከሩን አንስተዋል።

እንዲሁም የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ዝርያዎች ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመጠበቅ ማህበረሰቡን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግና ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን የባለስልጣኑ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አቶ ኩመራ ተናግረዋል።

ሐመረ ፍሬው

መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *