የማዳጋስካር ወታደራዊ መሪ ፕሬዝዳንት ሚካኤል አንድሪያኒሪና ፤በአዲሱ መንግስት ውስጥ ሚኒስትር ለመሆን የሚያመለክት ማንኛውም ሰዉ ከሙስና የጸዳ መሆኑን ለማረጋገጥ የውሸት መመርመሪያ /ፖሊግራፍ/ ምርመራ ይደረግበታል፡፡
ይህ እርምጃ ታይቶ የማይታወቅ የማጣሪያ ዘዴ ነው ተብሏል።
‹‹ሙሰኛው›› ማን እንደሆነ እና ማን ሊረዳን እንደሚችል በዚህ እናውቃለን ሲሉ አንድሪያኒሪና ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሀገሪቱ የፖሊግራፍ ማሽን እና ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ ባለሙያ አግኝታለች።
በምርመራው የወደቁ እጩዎች ‹‹ወደ ቃለ መጠይቅ አይሸጋገሩም›› ተብሏል። ምርመራውን ያለፉት ደግሞ ከፕሬዝዳንቱ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ይገናኛሉ።
እኛ የምንፈልገው መቶ በመቶ ንጹህ የሆነ ሰው ሳይሆን፤ ከ‹‹60 በመቶ››በላይ ንጹህ የሆነን ሰው ነው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
በልዩ የጦር ክፍል ውስጥ ኮሎኔል የሆኑት አንድሪያኒሪና፤በድህነት እና በዕድል እጥረት የተማረሩ ወጣት ማዳጋስካራውያን ለሳምንታት ባደረጉት ተቃውሞ ሳቢያ ባለፈው ጥቅምት ወር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊናን ከስልጣን ማውረዳቸው ይታወሳል።
ማዳጋስካር 32 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሀገር ናት።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት ሙሉ ካቢኔያቸውን ያሰናበቱ ሲሆን፤ እሁድ ዕለት ደግሞ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመዋል። በሁለት ዓመት ውስጥ ምርጫ ለማካሄድም ቃል ገብተዋል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 15/2018 ዓ.ም
