“ኢትዮጵያ ከ81 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ አድርጋለች” የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ እስካሁን ባከናወችው ጥረት ከ81.2 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች ሲሉ ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ተናገሩ፡፡

ከነዚህም ውስጥ ከ51 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በቢሾፍቱ በተከበረው የ2026 የዓለም የውሃ ቀን ላይ ካደረጉት ንግግር የሃገሪቱን ስኬቶችና ተግዳሮቶች ባቀረቡበት ክፍል ነው።

ለ81.2 ሚሊየን ዜጎች ከተዳረሰው የንጹህ ውሃ አገልግሎት ውስጥ ከ51 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች ሴቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ “ቁጥሩ ትልቅ ቢሆንም ገና በቂ አይደለም፤ በእያንዳንዱ መንደር ያሉ እናቶቻችንን ፍላጎት ለማሟላት በፍጥነት መንቀሳቀስ አለብን” ሲሉ በቀጣይ የሚጠበቀውን ስራ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር የሴቶችን የውሃ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራች ነው ሲሉም ዶ/ር ሀብታሙ አክለዋል

በታችኛው የውሃ ተቋማት አስተዳደር ረገድ የሴቶች ተሳትፎ 56 በመቶ መድረሱ ትልቅ ስኬት ነው ነው የሚሉት፡፡

ኢንጂነር ሀብታሙ፣ በምንጭ ልማትና በአካባቢ ጥበቃም የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

“በተለይም ባለፉት ሰባት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የተተከሉ 40 ቢሊየን ችግኞችን ከማፍላት ጀምሮ እስከ መትከል ድረስ አብዛኛውን ስራ የሰሩት ሴቶች ናቸው በማለት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በዘርፉ አሁንም ትልቅ ክፍተት መኖሩን ሚኒስትሩ አልሸሸጉም።

“በከፍተኛ አመራር ደረጃ፣ የውሃ ተቋማትንና ፕሮጀክቶችን በመምራት ረገድ እንዲሁም በዳይሬክተሮች ደረጃ የሴቶች ቁጥር አሁንም አነስተኛ ነው” ብለዋል።

ይህን ክፍተት መሙላት የዘርፉ ቀጣይ ትልቅ የቤት ስራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣይ እናቶችን እና እህቶችን ማዕከል ያደረገ የውሃ ልማት ስራን አጠናክሮ ይሰራል፤ የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚናንም ያሳድጋል በማለት ቃል ገብተዋል።

አዲስዓለም አበበ

መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *