በታይላንድ እና በኢራን መካከል በተደረገ ዲፕሎማሲያዊ ቅንጅት፤ አንዲት የታይላንድ የነዳጅ ጫኝ መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በሰላም ማለፏን የታይላንድ ባለሥልጣን እና የመርከቡ ባለቤት የሆነው የነዳጅ ኩባንያ ገልጸዋል።
ከከበባው ለመውጣትም ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልተጠየቀ ተረጋግጧል።
በባንግቻክ ኮርፖሬሽን ባለቤትነት የተያዘው ይህ መርከብ ስትራቴጂካዊ በሆነው የባህር መስመር ሰኞ ዕለት ያለፈው፤በታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኬው እና በታይላንድ የኢራን አምባሳደር መካከል ከተደረገ ውይይት በኋላ ነው።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ የታይላንድ መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፍ ካለባቸው፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እንዲኖር ሊረዱን ይችላሉ ወይ? ብዬ ጠይቄ ነበር” ብለዋል።
አክለውም “እነሱም ጉዳዩን እንደሚከታተሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ የሚያልፉትን መርከቦች ስም እንድንሰጣቸው ጠይቀውናል” ብለዋል።
በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚጓጓዘውን የዓለም አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት በማቋረጡ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሯል።
ግጭቱ የካቲት 21 ቀን ከተጀመረ ወዲህ፤ የታይላንድ መንግሥት የነዳጅ አቅርቦት በቂ ነው ቢልም፣ አገሪቱ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ እና በነዳጅ ማደያዎች ላይ ለሚታዩ ረጅም ሰልፎች ተጋልጣለች።
ይህ የታይላንድ የነዳጅ ጫኝ መርከብ በሰላም ማለፍ የቻለው፣ “ማዩሪ ናሪ” የተባለችው የታይላንድ የጭነት መርከብ በወሽመጡ ላይ በሚሳኤል ተመታ በደረሰባት የእሳት አደጋ ምክንያት ሠራተኞቹ መርከቧን ለቀው እንዲወጡ ከተገደዱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው።
እንደ ታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጻ፤ የኢራን እና የኦማን ባለሥልጣናት መርከቧ ወዳለችበት ቦታ የደረሱ ቢሆንም ታይላንድ አሁንም ስለጠፉት ሦስት የመርከቧ ሠራተኞች ሁኔታ መረጃ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ባንግቻክ ኩባንያ ባወጣው መግለጫ፤ ከመጋቢት 2 ጀምሮ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ላይ ቆማ የነበረችው መርከቡ አሁን ወደ ታይላንድ በመመለስ ላይ መሆኗን ገልጿል።
ለዚህም በታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኢራን ባለሥልጣናት መካከል የተደረገውን ስምምነት አድንቋል፡፡
ኩባንያው እና በታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ ምንጭ ነግሮኛል ሲል ሮይተርስ እንደዘገበዉ ለዚህ ሂደት ምንም ዓይነት ክፍያ አልተፈጸመም፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
