የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኢራን ላይ ለ48 ሰዓታት የሚቆይ ብርቱ የአየር ጥቃት (Blitzkrieg) እንዲሰነዘር ትዕዛዝ አስተላለፉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢራን ካቀረቡት የ15 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ጋር በተያያዘ በቴል አቪቭ በሚገኝ የምድር ውስጥ መሸሸጊያ (Bunker) ውስጥ ውጥረት የነገሰበት ስብሰባ ካደረጉ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ መረጃው ምንጮች ገለጻ፣ ኔታንያሁ የጦር ኃይላቸው በኢራን ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ኢላማዎች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ እንዲመቱ አዝዘዋል።
ይህ ትዕዛዝ የመጣው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለቴህራን የላኩትን የ15 ነጥብ የሰላም ስምምነት ሰነድ የእስራኤል ባለሥልጣናት ከመረመሩ በኋላ ነው።
ኔታንያሁ እና አማካሪዎቻቸው የትራምፕ ዕቅድ “የኢራንን ወታደራዊ አቅም ለመግታት በቂ አይደለም” በሚል ውድቅ አድርገውታል።
በስብሰባው ላይ የተገኙ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ እስራኤል ትራምፕ ከቴህራን ጋር ለዘላቂ ስምምነት ሊደርሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ስላደረባት፣ ስምምነቱ ከመጽናቱ በፊት ወታደራዊ እርምጃውን ለማጠናከር መርጣለች።
የትራምፕ የ15 ነጥብ ዕቅድ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እንድታፈርስ፣ የባሊስቲክ ሚሳኤል ክችቷን እንድትቀንስ እና በጎረቤት ሀገራት የሚገኙ ተላላኪ ቡድኖችን መርዳት እንድታቆም ይጠይቃል።
በምላሹም በኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች በሙሉ እንደሚነሱ ይገልጻል።ሆኖም ኢራን ይህንን የሰላም ጥሪ “የማይቀበሉት” መሆኑን በማስታወቅ ውድቅ ማድረጓ ተዘግቧል።
በአሁኑ ወቅት የእስራኤል አየር ኃይል በቴህራን እና በተለያዩ የኢራን ከተሞች ላይ ጥቃት መጀመሩ የተሰማ ሲሆን፣ አሜሪካም በበኩሏ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያሰማራች መሆኑ ታውቋል።
ቀጠናው ወደ ከፋ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ነግሷል።
ልዑል ወልዴ
መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
