30 ሺህ “የተደበቁ” የቲቢ ታማሚዎችን ለመፈለግ ቤት ለቤት አሰሳ እየተደረገ ነዉ መባሉንም ሰምተናል
በተለይም የቲቢ በሽታን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ እስካሁን በሕክምና ሥርዓት ውስጥ ያልተካተቱ 30 ሺህ “የተደበቁ” ታማሚዎችን ለማግኘት የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት ፍለጋ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እንደ ባለሙያዎች ማብራሪያ፤ በአገራችን ከሚከሰቱ የቲቢ አይነቶች መካከል 70 በመቶው ሳምባን የሚያጠቁ ሲሆኑ፤ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቁ ናቸው።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ህይወት ሠለሞን እንደገለጹት፤በሽታው በአየር አማካኝነት በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን፤ አንድ የታመመ ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ወቅት እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ጥቃቅን ጠብታዎችን ወደ አየር እንደሚለቅ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለ5 ደቂቃ ያህል ማውራት ብቻ እስከ 3 ሺህ የሚደርሱ በበሽታው የተበከሉ ጠብታዎችን ወደ አየር በማሰራጨት ሌሎችን ለበሽታው ሊያጋልጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ይህንን ስርጭት ለመከላከልም ሰዎች ሲያስነጥሱ ወይም ሲያስሉ አፍና አፍንጫቸውን በክንድ ወይም በማስክ የመሸፈን ልማድን ሊያዳብሩ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።
በሽታው በየዓመቱ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚሰጠው ትኩረትና ጥንቃቄ ግን አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል።
እስካሁን ባለው መረጃ 1መቶ50 ሺህ የቲቢ ታካሚዎችን ወደ ሕክምና ማዕከላት ማስገባት የተቻለ ሲሆን፤በህብረተሰቡ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ 30 ሺህ ተጨማሪ ታማሚዎችን የመለየት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታዉቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1ሺህ4መቶ60 አዳዲስ የሥጋ ደዌ ታማሚዎች ተለይተዋል።
በአሁኑ ወቅት 1ሺህ 8መቶ ሰዎች በሕክምና ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤በበሽታው ሳቢያ በዓመት እስከ 3ሺህ ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ ተመላክቷል።
ይህም የበሽታው ስርጭት ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 21 /2018 ዓ.ም
