ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) በኢትዮጵያ በዲጂታል ግብርና ዘርፍ ለተሰማራው “ለርሻ” (Lersha) የ1 ሚሊዮን ዶላር የሚቀየር የብድር ድጋፍ (Convertible Loan) ማድረጉን አስታወቀ።
ድጋፉ አነስተኛ አርሶ አደሮች የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ አባል የሆነው IFC ይፋ እንዳደረገው፤ ይህ የ1 ሚሊዮን ዶላር ብድር “ለርሻ” የዲጂታል አግሪ-ፋይናንስ መፍትሄዎቹን በስፋት ተደራሽ እንዲያደርግ ይረዳዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ340 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን እያገለገለ የሚገኘው ለርሻ፣ እ.አ.አ በ2030 የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ወደ 1 ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዱ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም IFC ከዳሸን ባንክ ጋር በመተባበር አርሶ አደሮች እና አነስተኛ የንግድ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል የጋራ ስጋት መጋሪያ (Risk-sharing facility) ስምምነት መፈራረሙ ታውቋል።
ይህም ዳሸን ባንክ ለአርሶ አደሮች የሚሰጠውን የብድር መጠን እንዲጨምር ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
እንደ IFC መረጃ፤ በአፍሪካ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በግብርና ላይ የተሰማራ ቢሆንም፣ ወደ ዘርፉ የሚፈሰው የንግድ ብድር ግን ከ5 በመቶ በታች ነው።
በመሆኑም እንዲህ ያሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትብብሮች ይህንን ከፍተኛ የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተመልክቷል።
ልዑል ወልዴ
መጋቢት 22/2018 ዓ.ም.
