በኢራን ጦርነት ወቅት ዓለም አቀፍ ሕግጋት መጣሳቸውን የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ

ከ100 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዎች በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ‹‹ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶችን››እየፈጸሙ መሆኑን በመጥቀስ ጥልቅ ስጋታቸውን የሚገልጽ ግልጽ ደብዳቤ ፈርመዋል።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የወሰኑት ውሳኔ ራስን ከመከላከል ውጭ ወይም በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ያልተፈቀደ ኃይል መጠቀም የሚከለከልበትን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በግልጽ የጣሰ ነው።

ባለሙያዎቹ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የኢራንን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ለማውደም የዛቱበትን ንግግር ጨምሮ በባለስልጣናት የሚነገሩ አስፈሪ ንግግሮችን ጠቅሰዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ ትራምፕ መላውን ቀጣና የበለጠ አስተማማኝ እያደረጉ ነው በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ባለሙያዎቹንም ‹‹ባለሙያ ነን ባዮች›› ሲል አጣጥሏቸዋል።

በደብዳቤው ላይ ባለሙያዎቹ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት ለጠላቶች ምንም አይነት ምህረት እንዳይደረግ የተናገሩትን ንግግር ተቃውመዋል።

በጦርነት ወቅት ምህረት አለመስጠት ማለት እጃቸውን የሰጡትን ወይም የቆሰሉትን ጨምሮ የማንንም ሰው ሕይወት ለመታደግ ፈቃደኛ አለመሆን ማለት ነው።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ምህረት እንደማይሰጥ ማወጅ በዓለም አቀፍ ሕግ በተለይ የተከለከለ ሲሆን፤ይህም ክልከላ በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የጦርነት ሕግ መመሪያ ውስጥም ተደንግጓል።

ባለሙያዎቹ በደብዳቤያቸው፤እዚህ የተጠቀሱት ድርጊቶች እና ዛቻዎች በሲቪሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ በመሆናቸው እንዲሁም የሕግ የበላይነትን እና የእያንዳንዱን ሀገር ሲቪሎች የሚጠብቁ መሰረታዊ መመሪያዎችን አደጋ ላይ እየጣሉ በመሆናቸው በእጅጉ ተጨንቀናል ብለዋል፡፡

አክለውም የከፍተኛ ባለስልጣናት ይፋዊ መግለጫዎች ሲቪሎችንም ሆነ የጦር ኃይሎችን የሚጠብቁትን የዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግጋት አለማክበርን ያሳያሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ዋይት ሃውስ በሰጠው መግለጫ፤የኢራን ባለስልጣናትን ላለፉት 47 ዓመታት አሜሪካውያንን በመግደል፣ ቁጥር አንድ የሽብር ስፖንሰር በመሆን እና ጨቋኝ አገዛዛቸውን የተቃወሙ የገዛ ዜጎቻቸውን በጭካኔ በመግደል ከስሷል፡፡

ትራምፕ ግን ‹‹ኢራን ለአሜሪካ እና ለወዳጆቿ የምታደርሰውን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስጋት በማስወገድ ቀጣናውን የበለጠ የተረጋጋ እያደረጉ ነው››ሲል ተሟግቷል።

ሂውማን ራይትስ አክቲቪስት ኒውስ ኤጀንሲ እንደገለፀው፤ ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ በኢራን 2መቶ44 ሕጻናትን ጨምሮ 1 ሺ 6መቶ6 ሲቪሎች ተገድለዋል፡፡

ሀና ሰይፉ

መጋቢት 25/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *