የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከምዕራብ አውሮፓ ጋር ግንኙነት ያለው መርከብ ሲያልፍ የመጀመሪያው ነው
ይህ የሆነው ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ቻይና የባህር ሰርጡን ለመክፈት የኃይል እርምጃን የሚፈቅደውን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ በተቃወሙ ማግስት ነው።
እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ፤ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነት ያለው ‹‹ሲ.ኤም.ኤ ሲ.ጂ.ኤም ክሪቢ››የተባለው የእቃ ጫኝ መርከብ ከሆርሙዝ የባህር ሰርጥ በስኬት ወጥቷል።
በፈረንሳዩ ግዙፍ የመርከብ ድርጅት የሚተዳደረውና የማልታ ሰንደቅ ዓላማ የያዘው ይህ መርከብ፤ በባህር ሰርጡ ማለፉ ተዘግቧል።
መርከቡ ወደ ኢራን ጠረፍ ተጠግቶ በቃሽም እና ላራክ ደሴቶች መካከል ባለው መስመር ያለፈ ሲሆን፤ የክትትል መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዛሬ ጠዋት በሙስካት የባህር ዳርቻ ደርሷል።
ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ፤ ኢራን የባህር ሰርጡን ለበርካታ ዓለም አቀፍ መርከቦች ዘግታው የነበረ ቢሆንም፤ይህ መርከብ የመጀመሪያው ምዕራባዊ ግንኙነት ያለው መርከብ ሆኗል።
መርከቡ ጉዞውን ከኢራን የባህር ኃይል ባለስልጣናት ጋር በመቀናጀት እንዳከናወነና የፈረንሳይ ባለቤትነት እንዳለው በግልጽ ሲያሳውቅ እንደነበር ተገልጿል።
ይህም ለተወሰኑ ዓለም አቀፍ መርከቦች በኢራን በኩል የተፈቀደ የጉዞ መስመር ሊኖር እንደሚችል ያመለክታል።
ይህ የተሳካ ጉዞ የተከናወነው ፈረንሳይ፣ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር በመሆን የባህር ሰርጡን ለመክፈት ወታደራዊ ኃይልን ጨምሮ ‹‹ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች››ለመውሰድ የቀረበውን የዩኤስ እና የአረብ ሀገራት የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙ በኋላ ነው።
ይህ የፈረንሳይ መርከብ በዚህ መስመር ቢጓዝም፤ ሌሎች ሶስት መርከቦች በኦማን የባህር ዳርቻ በሚገኝ የተለየና ደህንነቱ በተጠበቀ መስመር ቀደም ብለው መውጣታቸው ተገልጿል፡፡
ይህ ጉዞ በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ በኩል የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ዳግም መጀመሩን ቢያሳይም፤ ጉዞዎቹ ግን በኢራን ቁጥጥር እና ፈቃድ በተሰጣቸው አስተማማኝ መንገዶች ብቻ የሚከናወኑ መሆናቸውን ይጠቁማል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 25/2018 ዓ.ም
