ኢትዮጵያ የባህር በርን በሚመለከት የነበሩባትን ታሪካዊ ስህተቶች ለማረምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፋዊ እውቅና እያገኘ ነው ሲሉ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው “ባልተገባና በማንኛውም ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያት ሊደገፍ በማይችል ሁኔታ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
አቶ ዛዲግ እንዳሉት፣ ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በር ቁጥጥሩን ማጣቱ በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቁስል ጥሎ አልፏል። ከ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ጀምሮ፣ በ1993ቱ የሕወሃት ክፍፍል ወቅትም ሆነ በ1997ቱ ምርጫ፣ የባህር በር ጥያቄ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ቢቆይም፣ በተገቢው መንገድ ሳይመለስ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ትውልዱም የባህር በርን እንደ መሠረታዊ መብት ሳይሆን በገንዘብ እንደሚገዛ ተራ አገልግሎት እንዲቆጥረው ተደርጎ ቆይቷልም ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ያለው አመራር ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማረም በቆራጥነት እየሠራ ነው የሚሉት አቶ ዛዲግ፣ በአሁኑ ወቅት ተመዘገቡ ያሏቸውን ሁለት ዋና ዋና “ስኬቶችን” ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው ”ስኬት“ ያሉት፣ የባህር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ብሔራዊ አጀንዳ እንዲሆን መደረጉና ትውልዱ የባህር በር ለብልጽግና ያለውን ዋጋ እንዲረዳ መደረጉ ሲሆን፣ ሁለተኛውና “ትልቁ ስኬት” ሲሉ የገለጹት ደግሞ፣ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ማድረግ መቻሉ ነው።
“ከዓመት በፊት ስለ ባህር በር ማውራት እንደ ነውር ይታይ ነበር” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡና ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ጥያቄ ተገቢነት መረዳት መጀመራቸውንና “ጥያቄያችሁን ተረድተናል፣ ነገር ግን ጊዜ እንውሰድ” ወደሚል ንግግር መሸጋገራቸውን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በዲፕሎማሲያዊ ሥርዓትና በአመክንዮ የተደገፈ በመሆኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል በማለትም አሳስበዋል።
እንደ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ያሉ የባህር በር የሌላቸው ጎረቤት ሀገራትም የኢትዮጵያን ሕመም ተረድተው በጋራ እንዲቆሙ አቶ ዛዲግ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥንካሬ ካለና በዲፕሎማሲው መስክ በቁርጠኝነት ከተሠራ፣ ከ40 ዓመታት በፊት የተሠሩ ስህተቶችን በማረም ታሪክን ዳግም መጻፍ እንደሚቻል በንግግራቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።
አዲስአለም አበበ
ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም
