የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ሀገር ዉስጥ በሚገቡ አለምአቀፍ የዲጂታል መር ኩባንያዎች ዘርፉ ላይ እያሳዩ ባለዉ ፍላጎት ምክንያት ከገበያ የመዉጣት ስጋት ላይ ናቸዉ መባሉ ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነባር አሰራር በሚገቡት ኩባንያዎች እንዲዋጡ ፤ ከገበያ የሚወጡበት እና የሚገፉበት ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረገ ነዉ ተብሏል።
ይህ የተባለዉ በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር በኢንሹራንስ ዘርፉ ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ የጥናት ዉጤት በቀረበበት እና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመከረበት መድረክ ላይ ነዉ።
የጥናት ዝርዝሩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ያሬድ ሞላ የጥናቱን ግኝቶች አቅርበዋል።
ጥናት አቅራቢ አቶ ያሬድ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት በኢንሹራንስ ዘርፉ ሁለት ክስተቶች እየተፈጠሩ ይገኛል ብለዋል።
ይህንንም ሲያስረዱ በአለምአቀፍ ደረጃ የኢንሹራንስ ዘርፉ ቅርፁ በሰፊዉ እየተቀያየረ ይገኛል፤ ለዚህም አንዱ ምክንያት ዲጂታላይዜሽን መር አሰራር እየሰፋ መምጣት መሆን ይናገራሉ።
ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ የሚገኙ ትላልቅ የኢንሹር- ቴክ ኩባንያዎች እና ቢግ – ቴክ የሚባሉ ኩባንያዎች የኢንሹራንስ ዘርፉ ላይ ፍላጎት በማሳየት በአዲስ መልክ የኢንሹራንስ አገልግሎትን እየሰጡ ይገኛሉ ተብሏል።
አቶ ያሬድ እንደተናገሩት”ነባር ኩባንያዎች ከገበያዉ እየወጡ የሚገፉበት ሁኔታ በስፋት እየታየ ነዉ የመጣዉ” ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ የዲጂታል መር አሰራርን ባለመከተል ስራ እና ገበያ ከማጣታችን በፊት የደንበኞች የአገልግሎት ላይ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? የሚለዉን መመለስ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ ያሬድ ይህንን አዲስ የዲጂታል አሰራር መተግበር ያስፈልገናል ብለዋል።
ይህ ጥናት ኢትዮጵያ ዉስጥ በሚገኙ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተዉጣጡ ባለሙያዎችን ዕይታ የተጠየቀበት መሆኑን ጥናት አቅራቢዉ ተናግረዋል።
የዚህ ጥናት ግኝት እንዳመለከተውም የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፉ ከዲጃታላይዜሽን ጋር ያልተጣጠመ እና ደካማ እንዲሁም አነስተኛ መሆኑን አሳይቷል።
አቶ ያሬድ ይህ አሰራር በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ኩባንያዎቹ ችግር ላይ የሚወድቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ቁምነገር አየለ
ሚያዚያ 16/2018 ዓ.ም
