የማሊው መከላከያ ሚኒስትር ሳዲዮ ካማራ በባማኮ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ የመኪና ቦምብ ጥቃት ተገድለዋል።
ግድያው የተፈጸመው ሀገሪቱ ለሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ውጊያ እያስተናገደች ባለበት ወቅት ነው።
የቤተሰብ አባላት በሰጡት ቃል መከላከያ ሚኒስትሩ፣ ባለቤታቸዉ እና ሁለት የልጅ ልጆቻቸዉ በጥቃቱ ህይወታቸዉ ማለፉን አስታዉቀዋል፡፡ ይህም በስልጣን ላይ ላለው ወታደራዊ መንግስት ‹‹ትልቅ መርዶ›› ሆኗል ነዉ የተባለዉ።
ዓመጹ በመላ ሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎችን ኢላማ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም በሁለት ትልልቅ አማጺ ቡድኖች የሚመራ የተቀናጀ ጥቃት ነው።
አማፂያኑ ኪዳልን መቆጣጠራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የማሊ እንዲሁም የሩሲያ ድጋፍ ያላቸው ኃይሎች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የማሊ ጦር በሩሲያው የዋግነር ተዋጊዎች ድጋፍ ለዓመታት የዘለቀውን የአማፂያን ቁጥጥር በማክተም በ2023 ኪዳልን በቁጥጥሩ ስር አውሎ ነበር።
መንግስት ሁኔታው በቁጥጥር ስር መሆኑን ቢገልጽም ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ በርካታ ከተሞችን ካወከ በኋላ ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍርሃትና ድንጋጤ ውስጥ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
እስከዳር ግርማ
ሚያዚያ 19/2018 ዓ.ም
