የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ሞስኮ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ ለኢራኑ ከፍተኛ ዲፕሎማት ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ሩሲያ ሲደርሱ ባደረጉት ንግግር፤ ውጊያውን ለማቆም የሚደረጉ የሰላም ስምምነት ውይይቶች ላለመሳካታቸው ዋሽንግተንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ በወገኖቹ መካከል ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የሩሲያ የመንግስት ሚዲያ ፑቲን ለአራግቺ ‹‹በእኛ በኩል የእናንተን ጥቅም እንዲሁም የክልሉን ህዝቦች ጥቅም የሚያስከብር እና ሰላም በተቻለ ፍጥነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ማንኛውንም ነገር እናደርጋለን›› ማለታቸውን ዘግቧል።
ታስ የተሰኘው የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ፑቲን ‹‹የኢራን ህዝብ ለነፃነቱ እና ለሉዓላዊነቱ በምን ያህል ድፍረትእና ጀግንነት እየታገለ እንደሆነ›› አድንቀዋል።
የክሬምሊን መሪ አክለውም ሩሲያ ልክ እንደ ኢራን ስትራቴጂካዊ ግንኙነታችንን ለመቀጠል ፍላጎት አላት ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለሩሲያ የመንግስት ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፤አሜሪካ በአገራቸው ላይ በከፈተችው ጦርነት ካቀደቻቸው ግቦች ውስጥ ‹‹አንዱንም›› አላሳካችም ብለዋል።
ለድርድር የሚጠይቁትም ለዚህ ነው ያሉት ከፍተኛው ዲፕሎማት፤ እኛም አሁን ላይ ጉዳዩን እያጤን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አራግቺ በሴንት ፒተርስበርግ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተዋል።
ስለ ሩሲያ ድጋፍ የተጠየቁት ሚኒስትሩ “ኢራን እና ሩሲያ ስትራቴጂካዊ አጋሮች ናቸው” እና ሁለቱ አገሮች “ሁልጊዜም እርስ በርስ ይደጋገፋሉ” ሲሉ ብቻ ምላሽ ሰጥተዋል።
እስከዳር ግርማ
ሚያዚያ 20/2018 ዓ.ም
