የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለው ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ይፋ ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ እስከ 2025 አጋማሽ ድረስ ብቻ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል

ከ15 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ደግሞ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

ይህ የተገለጠው “አካል ጉዳተኝነት እና የአየር ንብረት ለውጥ፦ ለአፍሪካ ሁሉን ዓቀፍ እና ዘላቂ ምላሾችን መገንባት” በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 20 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ነው።

የኢትዮጵያን ናሽናል ዲስኤቤሊቲ አክሽን ኔትዎርክ (ENDAN)፣ ICCASA ከተባለ ተቋም ጋር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር አሸናፊ ሃይሉ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር እና ዘላቂ ልማት ባለሙያው ዶ/ር አሸናፊ ሃይሉ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ እያስከተለ ባለው አሳሳቢ ቀውስ ምክንያት እ.ኤ.አ እስከ 2025 አጋማሽ ድረስ ብቻ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ በፈረንጆቹ 2026 መጀመሪያ ላይ በሶማሊ ክልል ዶሎ አዶ የድንበር አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ለከፋ የውኃ እጥረት ተጋልጠዋል። በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የ64 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በርካቶች የደረሱበት አለመታወቁን ዶ/ር አሸናፊ አስታውሰዋል።

እነዚህ መሰል አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ደግሞ አካል ጉዳተኞች ዋነኛ ተጎጂዎች እንደሆኑ ተገልጿል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ 17.6 በመቶ (ከ15 ሚሊዮን በላይ) አካል ጉዳተኛ መሆኑ ቢገመትም፣ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሾች ግን ይህን የኅብረተሰብ ክፍል ያገለሉ መሆናቸውን ዶ/ር አሸናፊ ገልጸዋል።

ለአካል ጉዳተኞች ተጋላጭነት እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከልም፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቶች መስማት እና ማየት ለተሳናቸው ሰዎች በሚመች መልኩ አለመዘጋጀታቸው፣ የአደጋ ጊዜ መጠለያዎች እና የማምለጫ መንገዶች ምቹ አለመሆናቸው እንደሚገኙበት ተነስቷል።
በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች ካላቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የተነሳ አደጋን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ማጣታቸው ሌላኛው ለተጋላጭነታቸው የተጠቀሰ ምክንያት ነው፡፡

ችግሮቹን ለመቅረፍ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ትግበራ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡ በማንኛውም ብሔራዊ የአየር ንብረት ፖሊሲ አካል ጉዳተኝነትን ታሳቢ ቢደረግ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች በድምፅ፣ በምስል እና በቀላል ቋንቋ ተደራሽ ቢሆኑ ችግሩን ለማቃለል መፍትሔ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም፣ መንግስት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት እንዲሰሩና በመረጃ አሰባሰብ ወቅት አካል ጉዳተኝነትን የለየ ጥራት ያለው መረጃ እንዲያዝ ጥሪ ቀርቧል።

አዲስአለም አበበ

ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *