በደቡብ ሱዳን እየተባባሰ የመጣው ግጭትና መፈናቀል ያስከተለውን ሰብአዊ ቀውስ ተከትሎ፣ ከሀገሪቱ ሕዝብ 56 በመቶው ወይም 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት አመለከተ።
የተባበሩት መንግሥታት የግብርና ድርጅት ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ዩኒሴፍ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ሊቀለበስ የማይችል ሰብአዊ ጥፋት ከመከሰቱ በፊት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ሪፖርቱ በተለይ በሕጻናት ላይ ያለው አደጋ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሶ፣ 2.2 ሚሊዮን ሕጻናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጋለጣቸውንና 700 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት በሚያደርስ አደጋ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።
ለዚህ ቀውስ ዋነኛ መንስኤ ናቸው ተብለው የተጠቀሱ ደግሞ ቀጣይነት ያለው የጎሳ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ ከጎረቤት ሱዳን የሚፈሰው የጦርነት ስጋትና ስደተኞች ናቸው።
በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትል ፕሬዝዳንት ሪያክ ማቻር መካከል ያለው የቆየ ቅራኔ ዳግም አገር አቀፍ የእርስ በርስ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚለው ስጋትም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ይህም ቀደም ሲል ለተጎዱ የሕክምናና የምግብ እርዳታ ማዕከላት ሥራ መስተጓጎል ዋና ምክንያት ሆኗል።
ሳራ ዮሀንስ
ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም
