የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ5 ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ደንበኞች ወደ ዘመናዊ የቆጣሪ ሥርዓት ለማሸጋገር ማቀዱን ገለጸ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ያልሆኑ (ሜካኒካል) ቆጣሪ የሚጠቀሙ 4.64 ሚሊዮን ደንበኞቹን ጨምሮ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ ዘመናዊ የቅድመ ክፍያ እና ስማርት ቆጣሪዎች ለመቀየር ማቀዱን አስታወቀ።

የተቋሙ የማርኬቲንግ ሽያጭና የደንበኞች አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳይያስ ደንድር እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ካሉት 5.64 ሚሊዮን ደንበኞች መካከል አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ዘመናዊ ቆጣሪ ተጠቃሚዎች ናቸው። ቀሪዎቹን 4.64 ሚሊዮን ደንበኞች ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማሸጋገር በታቀደው መሠረት፤ ደንበኞች በቤታቸው ወይም በሥራ ቦታቸው ሆነው በሞባይል ስልካቸው ክፍያ መፈጸም የሚያስችላቸው ይሆናል።

ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ለነባር ደንበኞች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የስርጭት ኔትወርክ ጥገናና የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
አዲስ ኃይል ለማግኘት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ቀደም ሲል ሳምንታትና ወራትን ይፈጁ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኢሳያስ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ “ኤሌክትሪክ በአንድ ቀን” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው ዘመቻ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ አዲስ ኃይል ከተገናኘላቸው 415 ሺህ ደንበኞች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በ10 ቀንና ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 800 ሺ አዲስ ሃይል ለማገኛኘት ዕቅድ አድርገን ነው የተነሳነው ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ ለዚህም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማለትም ቆጣሪዎች፣ ኬብሎችና ሰርኪውት ብሬከሮች እንዲሟሉ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ቆጣሪዎችን ማገናኘት የቻለ ቢሆንም፣ እያደገ ከመጣው የማህበረሰቡ ፍላጎት አንጻር በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ለማገናኘት እየሠራ መሆኑ ተመልክቷል።

አዲስአለም አበበ

ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *