በግል ድርጅቶች ዉስጥ አነስተኛ መዋጮ እየተሰበሰበ፤ ከፍተኛ የጡረታ አበል እየተወሰነ መሆኑ የጡረታ ፈንዱን ዘላቂነት ስጋት ዉስጥ ጥሏል ተባለ

አንዳንድ ድርጅቶች ባልተገባ መንገድ ደሞዝን አሳንሶ በማሳወቅ የሚከፈል የጡረታ መዋጮ በአሰባሰብ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝም ተነግሯል።

የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ203 ሺህ በላይ አዳዲስ ሠራተኞችን እና ከ30 ሺህ በላይ ድርጅቶችን የዐቅዱ አባል ማድረጉን አስታውቋል ።

አስተዳደሩ የባለመብቶች ተጠቃሚነትን በተመለከተ በአገልግሎት(በዕድሜ )በጤና ጉድለት፣ በሥራ ላይ ጉዳት እና በሞት ለተተኪዎች በአጠቃላይ ለ5 ሺህ 3 መቶ 17 ባለመብቶች የጡረታ አበል ውሳኔ እንደሰጠም በሪፖርቱ ጠቁሟል።

ከመዋጮ አሰባሰብ እና ከድርጅት ምዝገባ ጋር በተያያዘ አስተዳደሩ ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን ከሪፖርቱ ተመልክተናል ።

በአንዳንድ ድርጅቶች ባልተገባ መንገድ ደሞዝን አሳንሶ በማሳወቅ የሚከፈል የጡረታ መዋጮ በአሰባሰብ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብሏል አስተዳደሩ።

ከዚህ በተጨማሪ አነስተኛ መዋጮ እየተሰበሰበ ከፍተኛ የጡረታ አበል እየተወሰነ መሆኑ የጡረታ ፈንዱን ዘላቂነት ላይ ስጋት ላይ መጣሉ በአስተዳደሩ በችግርነት ተነስቷል።

የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አባተ ምትኩ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እስኪስተካከል ድረስ ድርጅቶች ታክስ የከፈሉበትን ትክክለኛ የደሞዝ መጠን በማየት የጡረታ መዋጮውም በዚያው ልክ እንዲከፈል ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ በሪፖርቱ የግምገማ መድረክ ላይ አሳስበዋል።

በባለፉት ዘጠኝ ወራት አስተዳደሩ በገቢ አሰባሰብ 39.7 ቢሊዮን ብር የጡረታ መዋጮ የተሰበሰበ መሆኑ ተነግሯል።

ከኢንቨስትመንት ብር 16.9 ቢሊዮን ብር የግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ትርፍ ማግኘት መቻሉንም በሪፖርቱ ጠቁሟል።

ቁምገር አየለ

ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *