እነዚህ ማዕከላት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በ13.7 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ ናቸው።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ እንዳስታወቁት፥ማዕከላቱ በከተማዋ ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲሰፍን የኑሮ ውድነትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
እንደ ወይዘሮ ሀቢባ ገለፃ፥ ከተማዋን በሚመጥኑ አምስት አማካኝ ቦታዎች ላይ የተገነቡት እነዚህ ግዙፍ ማዕከላት ገበያውን ከህገ-ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት በማጽዳት ረገድ ውጤታማ ሆነዋል።
አገልግሎት መስጠት የጀመሩት እነዚህ ማዕከላትም የላፍቶ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ሁለገብ የገበያ ማዕከላት፣ የአቃቂ ሁለገብ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል፣ የኮልፌ ሁለገብ ዘመናዊ የግብርና ምርቶች ማዕከል፣ የሰሚት ሁለገብ የገበያ ማዕከል እና የለሚ ኩራ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት መሆናቸው ተገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የግንባታ ቦታዎችን በመወሰንና ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለዘመናዊ የንግድ ስርዓት መስፈን ትልቅ ድጋፍ ማድረጉን ኃላፊዋ አብራርተዋል።
ማዕከላቱ የግብርና ምርቶችን ለሸማቾች በአቅራቢያቸው ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በውስጣቸው የባንክ፣ የወፍጮ፣የካፍቴሪያ እና ሌሎች አገልግሎቶችን አካተው በመያዛቸው ለሸማቹ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም እነዚህ ማዕከላት ከመላው ሀገሪቱ ለተውጣጡ አምራቾች በግልፅ ጨረታ ተላልፈው እንዲሰሩ በመደረጉ ከመደበኛው ገበያ አንጻር ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
አቤል እስጢፋኖስ
ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም
