የኢራን ጦርነት  ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች እና ባንኮች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ እንዲያጋብሱ እያደረገ ነው

በኢራን ውስጥ እየተካሄደ ያለው የዩኤስ-እስራኤል ጦርነት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ላይ የኢኮኖሚ ጫና እያሳደረ ባለበት በዚህ ወቅት ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ታሪካዊ የተባለ ከፍተኛ ትርፍ እያስመዘገቡ መሆኑ ተሰምቷል።

ጦርነቱን ተከትሎ ኢራን ስትራቴጂካዊ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ  (Strait of Hormuz) መዝጋቷ የዓለምን የኃይል አቅርቦት በእጅጉ ያወከ ሲሆን፣ ይህም ለነዳጅ ኩባንያዎች እና ለትላልቅ ባንኮች የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል።

ከዓለም የነዳጅና የጋዝ አቅርቦት ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የሚያልፍበት የሆርሙዝ የባህር መስመር ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ መዘጋቱ በገበያው ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል ነገር ግን የዋጋ መዋዠቁን  እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙት የአውሮፓ የነዳጅ ኩባንያዎች የትርፍ መጠናቸው በእጥፍ ጨምሯል።

ቤፒ(BP)  በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 3.2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

በተጨማሪም  ሼል 6.92 ቢሊዮን ዶላር ሲያተርፍ፣ የፈረንሳዩ ቶታል ኢነርጂስ ደግሞ ትርፉን በ33 በመቶ በማሳደግ 5.4 ቢሊዮን ዶላር አድርሷል።

ምንም እንኳን እንደ ኤክሶን ሞቢል እና ቼቭሮን ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአቅርቦት መቆራረጥ ምክንያት ገቢያቸው መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳይም፣ አሁንም በከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ምክንያት የትርፍ ግምታቸው እያደገ መሆኑ ተመልክቷል።

በፋይናንሱ ዘርፍም “ቢግ ሲክስ” (Big Six) በመባል የሚታወቁት ስድስቱ ግዙፍ የአሜሪካ ባንኮች በጦርነቱ ሳቢያ በፈጠረው የገበያ መነቃቃት ከፍተኛ ገቢ አግኝተዋል።

ባንኮቹ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ በአጠቃላይ 47.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አስመዝግበዋ በተለይም ጄፒ ሞርጋን (JP Morgan) በታሪኩ ሁለተኛውን ከፍተኛ የሩብ ዓመት ትርፍ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ባለሀብቶች ከስጋት ነፃ የሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ፍለጋ የሚያደርጉት ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር መሆኑ ተገልጿል።

ከነዳጅና ከባንክ ባሻገር፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪው የጦርነቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሆኗል ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ተንታኞች እንደሚሉት የኢራኑ ግጭት በአየር መከላከያ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በማሳየቱ  ምዕራባውያን መንግስታት በሚሳኤል መከላከያ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (Drones) ላይ የሚያወጡትን በጀት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምሩ አስገድዷቸዋል።

ባጠቃላይ ጦርነቱ በዓለም ዙሪያ የኑሮ ውድነትን እያባባሰ የተራ ዜጎችን ኑሮ እያመሰቃቀለ ባለበት ሁኔታ፣ ጥቂት ኩባንያዎች ግን ከጦርነቱ ድምፅ በስተጀርባ ታላቅ የንግድ ስኬት እያከበሩ ይገኛሉ።

ሀና ሰይፉ

ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *