በኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃና አስተዳደር ሥርዓት ላይ የግንዛቤ እጥረት ትልቅ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ እንደገለጹት፤ ኅብረተሰቡ ለአእምሯዊ ንብረት ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆንና የፈጠራ ውጤቶችን እንደ ሀብት የመቁጠር ዝንባሌ አናሳ መሆን ለፈጠራ ባለሙያዎች መብት መከበር ዋነኛው እንቅፋት ሆኗል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ባለሥልጣኑ ነባር የንግድ ምልክት፣ የፓተንትና የቅጂ መብት ሕጎችን የማሻሻልና ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር የማጣጣም ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም በባሕር ዳር፣ በጅማ እና በሀዋሳ ከተሞች የሳተላይት ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት ወደ ሥራ ገብቷል ያሉ ሲሆን፣ ከፖሊስና ከፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀትም የሕግ ማስከበር አቅምን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የፈጠራ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂና የሥልጠና ድጋፍ እንዲያገኙም ከዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ሐመረ ፍሬው
ግንቦት 04/2018 ዓ.ም
