የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሰኞ ዕለት ኢራን ወደ ቻይና የምታደርገውን የነዳጅ ጭነት በማገዝ በጠረጠራቸው በሦስት ግለሰቦች እና በዘጠኝ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።
ከእነዚህም መካከል አራቱ በሆንግ ኮንግ፣ አራቱ ደግሞ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ዘጠነኛው ኩባንያ ደግሞ በኦማን የሚገኝ ነው።
ይህ የዩኤስ የግምጃ ቤት እርምጃ የተወሰደው፣ ለድሮን እና ለባሊስቲክ ሚሳኤሎች መሥሪያ የሚያገለግሉ የጦር መሣሪያዎችንና አካላትን በመግዛት ለኢራን ድጋፍ በሚያደርጉ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ላይ ዓርብ ዕለት ከተጣለው ማዕቀብ ቀጥሎ ነው።
ማዕቀቡ የተጣለው የዩኤስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሺ-ጂን ፒንግ ጋር ለማድረግ ካቀዱት ስብሰባ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።
በዚህ ስብሰባ ላይ ትራምፕ የቻይናው መሪ ከኢራን ጋር ያለውን ውጥረት ለመፍታት እና ወሳኙን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዳግም ለማስከፈት እንዲረዱ ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ሀብት ቁጥጥር ቢሮ (OFAC) ያወጣቸው አዳዲስ ስያሜዎች፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጦር የተለያዩ ሽፋን ያላቸው ኩባንያዎችን በመጠቀም የኢራንን ነዳጅ ወደ ቻይና እንዲሸጥና እንዲያጓጉዝ የረዱ ግለሰቦችንና ተቋማትን ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን የግምጃ ቤት መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
የግምጃ ቤት ጸሐፊ ስኮት ቤሰንት እንደተናገሩት፣ የትራምፕ አስተዳደር የኢራን መንግሥት እና ወታደራዊ ኃይል ለጦር መሣሪያ፣ ለኒውክሌር መርሃ ግብር ወይም በክልሉ ለሚገኙ ተላላኪ ቡድኖች የሚያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረቅ በማዕቀብ መጠቀሙን ይቀጥላል።
ሃና ሰይፉ
ግንቦት 04/2018 ዓ.ም
