የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከዚህ ቀደም ድንበር ተሻግረው በሚመጡ ታጣቂዎች ምክንያት የወርቅ ማዉጣት ሂደት ላይ ችግሮች እንደገጠሙት ተነግሮ ነበር።
ክልሉ ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም ከኬንያ በሚመጡ ታጣቂዎች በህገወጥ የወርቅ ማዉጣት ላይ መሳተፍን ጨምሮ በአካባቢው ላይ ዘረፋ ተፈፅመዋል የሚል መረጃ ተነግሯል።
ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የማእድን እና ኢነርጂ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸዉ ወልያብ፤ አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ድንበር ተሻጋሪ ታጣቂዎች በህገወጥ ወርቅ ማዉጣት ላይ ሲሳተፉ አላገኘንም ፥ ያየነዉም ነገር የለም ብለዋል።
አቶ ጌታቸዉ እንደሚገልፁት “ሆኖም የማዕድን ማዉጫ ቦታዎቹ በወረዳዎች ዉስጥ ናቸዉ ፤ በማህበራት እና በግዥ ስርአት ላይ ህገ ወጥ የማዕድን ማዉጣቱ ነገር ይስተዋላል ” ሲሉ ተናግረዋል።
የህገወጥ ማወጣት እና ዝዉዉሩን ለመግታት ከፍቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር ስራ ጋር ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ ነዉ ሲሉ ክልሉ ገልጿል።
ክልሉ በባለፉት ዘጠኝ ወራት በወርቅ ምርት ላይ እንዲሰማሩ ለ 2 መቶ 2 አዲስ አልሚዎች ፍቃድ እንደሰጠ አቶ ጌታቸዉ ነግረዉናል።
ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ግብይቱ በተደራጁ ማዕከላት ብቻ እንዲሆን መደረጉን ሰምተናል።
በክልሉ አሁን ላይ ወርቅ እና የድንጋይ ከሰል ብቻ እየወጣ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በወርቅ ደረጃ ለማዕከላዊ ባንኩ 3 መቶ 2 ነጥብ 276 ኪሎግራም ወርቅ ማስገባቱን የክልሉ የማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።
አክለውም 1 መቶ 22ሺህ 8መቶ 90 ቶን የድንጋይ ከሰልን ማምረት ተችሏል ብለዋል።
ቁምነገር አየለ
ግንቦት 04/2018 ዓ.ም
