ጋና 300 ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ ልታስወጣ ነው


ጋና በቅርቡ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የተነሳውን የተቃውሞ  ተከትሎ 300 ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ እንደምታስወጣ አስታውቃለች።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ ማክሰኞ ዕለት በኤክስ (X) ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የጋና ፕሬዝዳንት ዜጎቹ “በአስቸኳይ እንዲወጡ” ፈቃድ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
 
ሚኒስትሩ እንዳሉት “ጭንቅ ላይ የወደቁት” ጋናውያን ለመውጣት በፕሪቶሪያ በሚገኘው ኤምባሲ ተመዝግበዋል።
 
ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት በስፋት የተሰራጩት ቪዲዮዎች ሀሰተኛ ናቸው ብለዋል። ሰኞ ዕለት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በውጭ ዜጎች ላይ የሚሰነዘሩት “ተቃውሞዎች እና የወንጀል ድርጊቶች” የመንግስትን ፖሊሲ እንደማያንፀባርቁ ገልጸው፣ ድርጊቶቹን ” የወንጀል ድርጊቶች” በማለት ገልጸዋቸዋል።
 
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ደቡብ አፍሪካ “ስደትን እንደምትቆጣጠር፣ ድንበሮቿን እንደምታስከብር እና ህጎቿን እንደምታስፈጽም” ተናግረዋል።
 
በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ህገ-ወጥ ስደትን በመቃወም ሰልፍ የወጡ ሲሆን፣ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች በጅምላ እንዲባረሩ ጠይቀዋል። ተቃዋሚዎቹ ህገ-ወጥ ስደት በስራ ዕድል፣ በመኖሪያ ቤት እና በወንጀል መጠን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ይላሉ።
 
ማክሰኞ ዕለት በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የጋና ኤምባሲ ዜጎቹ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ከሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች እንዲርቁ እና ረቡዕ ዕለት በደርባን የወደብ ከተማ ከታቀደው ተቃውሞ በፊት ሱቆቻቸውን ወይም የንግድ ቦታዎቻቸውን በመዝጋት ለደህንነታቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ መክሯል።
 
ጋና እና ናይጄሪያ በቅርቡ የደቡብ አፍሪካን አምባሳደሮች በመጥራት በዜጎቻቸው ላይ እየደረሰ ስላለው እንግልት እና ትንኮሳ ማብራሪያ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ጋና ለአፍሪካ ህብረት (AU) በጻፈችው ደብዳቤ ጉዳዩ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አፍሪካውያን ደህንነት ላይ “ከፍተኛ አደጋ” እየደቀነ በመሆኑ ውይይት እንዲደረግበት ጠይቃለች።
 
ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ “የምትደብቀው ነገር የለም” በማለት ምላሽ ሰጥታለች። መንግስት “ሀሰተኛ ቪዲዮዎች እና ምስሎች” ሲል የጠራቸውንና አንዳንዶች በውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው ብለው የጠሰራጩትን  ምስሎች አውግዟል።
 
ኢትዮጲያ ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሌሶቶ እና ዚምባብዌ ዜጎቻቸውን ካስጠነቀቁ ሌሎች ሀገራት መካከል ይገኙበታል።
 
እንደ ይፋዊ መረጃዎች ከሆነ ደቡብ አፍሪካ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች መኖሪያ ስትሆን፣ ይህም ከጠቅላላው ህዝብ 5 በመቶውን ይይዛል። ሆኖም ሰነድ የሌላቸው ሌሎች በርካታ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናል። የውጭ ዜጎች ጥላቻ (Xenophobia) በሀገሪቱ ውስጥ የቆየ ችግር ሲሆን፣ አልፎ አልፎም ገዳይ የሆኑ ጥቃቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል ይላል የቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ።
 
ግንቦት 06/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *