አቃቤ ህግ በጋዳፊ ጉዳይ በሳርኮዚ ላይ የሰባት ዓመት እስራት ጠየቀ

የፈረንሳይ አቃቤ ህግ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ በ2007 ላደረጉት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ከሙአመር ጋዳፊ ህገ-ወጥ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል በሚል ክስ፣ በይግባኝ ችሎቱ የሰባት ዓመት እስራት እንዲወሰንባቸዉ ጠይቋል።

ይህ ጉዳይ በፈረንሳይ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ መነጋገሪያ ከሆኑ የፖለቲካ እና የፋይናንስ ቅሌቶች አንዱ ሆኗል።

አቃቤ ህግ ‹‹ብርቱ›› ሲል የገለጸውን የመዝጊያ ክርክር ለሦስት ቀናት ካቀረበ በኋላ፤ የፓሪስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ በዋናው የፍርድ ቤት ሂደት ወቅት የጠየቀው የሰባት ዓመት እስራት በይግባኝ ችሎቱም እንዲጸድቅ ጠይቋል።

ሳርኮዚ ቀደም ሲል ጥፋተኛ ተብለው የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም፤ይግባኝ እስከሚጠይቁ ድረስ ለ20 ቀናት ብቻ በእስር ላይ ቆይተው ተለቀው ነበር።

አቃቤ ህግ ሳርኮዚን ለ2007ቱ የምርጫ ቅስቀሳቸው ድብቅ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከሊቢያው አገዛዝ ጋር የተደረገውን ስምምነት “ዋነኛ፣ ብቸኛ ተጠቃሚ” እና “አቀነባባሪ” እንደሆኑ አድርጎ አቅርቧቸዋል።

አሁን ወደ ማጠናቀቂያው የተቃረበው የይግባኝ ችሎት ‹‹አንዲት ሳንቲም እንኳ›› የሊቢያ ገንዘብ ለምርጫ ቅስቀሳዬም ሆነ ለግል ጥቅሜ አልገባም ለሚሉት ሳርኮዚ ወሳኝ ነው።

በድጋሚ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ፣ የቀራቸው ብቸኛ የህግ አማራጭ ለፈረንሳዩ የሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማቅረብ ብቻ ይሆናል።

የሳርኮዚ ጠበቃ ክሪስቶፍ ኢንግሬን የሊቢያ የገንዘብ ድጋፍ ክስን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም በማለት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ‹‹ፍጹም ንፁህ››መሆናቸውን መከላከያቸው እንደሚያስረዳ ገልጸዋል።

እስከዳር ግርማ

ግንቦት 06/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *