በተለይም በዋና መንገዶች ላይ በህገወጥ መንገድ ማስታወቂያ የመለጠፍ ድርጊትን በካሜራ በታገዘ መልኩ ቁጥጥር እያደረኩ እገኛለሁ ሲል የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግሯል።
ማስታወቂያን በዲጂታል መንገድ ብቻ የማድረግ ግዴታ መጣሉን ተከትሎ በፖሎች ላይ ማስታወቂያ መስቀልም ሆነ መለጠፍ መከልከሉ ይታወቃል።
የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የምስራች ግርማ እንደሚገልጹት፥ የህገወጥ ማስታወቂያ መስቀል እና መለጠፍ ድርጊቶች ሙሉ ለሙሉ አልቀሩም።
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በባለፉት ዘጠኝ ወራት ሲያደርግ በቆየዉ ቁጥጥር ከ10 ሺህ በላይ ህገወጥ ማስታወቂያዎችን ማንሳቱን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ነግረዉናል።
አቶ የምስራች አያይዘውም የማስታወቂያዎቹን ባለቤቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህ የተጠያቂነት ደረጃም ማስታወቂያዎች የሚለጥፉ ላይ ብቻ ሳይሆን የሚያባዙ የህትመት ቤቶች ጭምር ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
የደንብ ማስከበር ባለስልጣን እስከ ምሽት 4 ሰአት የሚሰራ በመሆኑ ሌሊት ላይ ማስታወቂያን የሚለጠፉ እንዳሉም የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ የምስራች ገልፀዋል።
ከህገወጥ ድርጊቶች ጋር ተያይዞ የባለስልጣኑ የነፃ የስልክ መስመር በቀን ከ3 መቶ በላይ የህብረተሰብ ጥቆማ እየደረሰዉ መሆኑን ባለስልጣኑ ተናግሯል።
በአዲስ አበባ ዋና መንገዶች ላይ በሚገኙ ካሜራዎች በመታገዝ ህገወጥ ማስታወቂያዎች ሲለጠፉ ለሚመለከተዉ ክፍለከተማ እና ወረዳ ጥቆማ እንዲደረግ የቴክኖሎጂ ስርዓት መዘርጋቱን አቶ የምስራች አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስታወቂያዎችን ለማዘመን በሚል የቢልቦርድ ማስታወቂያዎች እንዲነሱ መመሪያ መዉጣቱ እንዲሁም በዲጂታል ስክሪኖች እንዲተኩ መደረጉ ይታወሳል።
ቁምነገር አየለ
ግንቦት 14/2018 ዓ.ም
