የአሜሪካ ጦር በደቡባዊ ኢራን ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን መፈጸሙን ያስታወቀ ሲሆን፥ ጥቃቶቹ የኢራንን ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ጣቢያዎችን እና ፈንጂዎችን ለመቅበር የሚሞክሩ ጀልባዎችን ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጿል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፥ ጥቃቶቹ የተፈጸሙት “ራስን ለመከላከል” መሆኑንና በኢራን ኃይሎች ሊሰነዘሩ ከሚችሉ ዛቻዎች ወታደሮቻችንን ለመጠበቅ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቲም ሃውኪንስ እንደተናገሩት፥ የአሜሪካ ጦር በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ራስን የመግታት እርምጃ እየወሰደ ኃይሎቹን መከላከል ይቀጥላል ብለዋል።
ጥቃቶቹ የተፈጸሙት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋኢ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ የተወሰነ መሻሻል መታየቱን፣ ነገር ግን ግጭቱን ለማቆም የሚደረገው ስምምነት “አሁን ተቃርቧል” ማለት እንዳልሆነ በተናገሩበት ወቅት ነው።
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፥ ካፒቴን ሃውኪንስ ጥቃቶቹ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ የምትገኘውንና የኢራን የባህር ኃይል እዝ መቀመጫ የሆነችውን ባንዳር አባስ የተባለችውን የደቡብ የወደብ ከተማ አቅራቢያ ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢራን የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ቀደም ሲል እንደዘገቡት፥በባንዳር አባስ ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ የአካባቢው ባለስልጣናት ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ነበር።
ኢራን እስካሁን ላለፉት አዳዲስ የአሜሪካ ጥቃቶች ምላሽ አልሰጠችም።
ጥቃቶቹ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ሊደረግ በሚችለው የሰላም ስምምነት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ከጥቃቶቹ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስምምነት ላይ መድረስ አሁንም እንደሚቻል ገልጸው፥ማክሰኞ ዕለት በኢራን ዋና ተደራዳሪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም በኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የሚደረግ ውይይት መኖሩን ጠቁመዋል።
ሀና ሰይፉ
ግንቦት 18/2019 ዓ.ም
