ናታኒያሁ እስራኤል “ከሂዝቦላህ ጋር ጦርነት ላይ ነች” አሉ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታኒያሁ ሀገራቸው በሂዝቦላህ ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንደምታጠናክር ካስታወቁ በኋላ፣ የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ላይ አዲስ የጥቃት ማዕበል መጀመሩን ገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል (IDF) በምስራቅ ሊባኖስ በሚገኘው በቤካ ሸለቆ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የሂዝቦላህ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መክፈቱን አስታውቋል።

በኢራን የሚደገፈው እና በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሺዓ ሙስሊም ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ በበኩሉ፣ 22 የድሮን እና የሮኬት ጥቃቶችን በመሰንዘር የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን ገልጾ፣ ኢላማዎቹም የእስራኤል ወታደሮች፣ ታንኮች፣ የጦር ሰፈሮች እና ህንፃዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሊባኖስና እስራኤል ለ45 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማራዘም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ጥቃቱች ግን መቀጠላቸው ተሰምቷል።

ናታኒያሁ ሰኞ ምሽት ባስተላለፉት የቪዲዮ መግለጫ እስራኤል “ከሂዝቦላህ ጋር ጦርነት ላይ ነች” ያሉ ሲሆን፣ ወታደራዊ ኃይሉም “ብርቱና አደቀቂ ምት እንዲያሳርፍባቸው” መታዘዙን ተናግረዋል።

ናታኒያሁ እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ “ከ600 በላይ አሸባሪዎችን መደምሰሷን” ገልጸዋል።

በመቀጠልም “ነገር ግን ይህ አሁን ከእኛ የሚፈልገው ጥቃቱን ማጠናከር እና መጠኑን (ሃይሉን) መጨመር ነው” ብለዋል ሲል ቢቢሲ ዘገቧል።

ሁለቱ የእስራኤል የቀኝ ክንፍ ጽንፈኛ ሚኒስትሮች ቤዛሌል ስሞትሪች እና ኢታማር ቤን ጊቪር ወታደራዊ ዘመቻው ቤሩትን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች እንዲሰፋ ጥሪ አቅርበዋል።

ግንቦት 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *