ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት መጠናቀቁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማሩ ጃኔበሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ምርጫው ግልጽነት እና ፍትሐዊነት ከመላበሱም ባሻገር በመራጩ የከተማዋ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቅቡልነት ያሳየ ነው።
ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት ለምርጫው ስኬታማነት መሥራቱን አስታውሰው፤ ይህም ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ለፓርቲዎች የሰጡት የአየር ሰዓት ፍትሐዊ፣ ግልጽና ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ የሰጠ ነው ያሉት አቶ ማሩ፤ ይህም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ያሉትን ፖሊሲና አማራጭ ሀሳቦች ያለምንም ገደብና ጫና ለሕዝቡ የሚያቀርብበት ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
የድምጽ ቆጠራውና ውጤቱን የማደራጀት ሥራ የሚያከናወነው በሕጉ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በመሆኑም ውጤቱ በከተማ ደረጃ በኦፊሴላዊ መልኩ እስኪገለጽ ድረስ በትዕግስት እንዲጠበቅ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል ነው ያሉት።
የምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የሕዝብ ድምጽ ልናከብር ይገባል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ የሰለጠነና ብስለት የተሞላበት የፖለቲካ አካሄድም ይሄው መንገድ ነው ብለዋል።
ግንቦት 25/2018 ዓ.ም
