አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች በጋራ በመሆን የግብርና ቢዝነስ ኩባንያዎችን እንዲያቋቁሙና የፋብሪካ ባለቤቶች እንዲሆኑ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
አዋጁ አርሶ አደሩን ከደላላ ተጽዕኖ ነፃ በማውጣት፣ ጉልበትና መሬቱን ወደ ካፒታል እንዲቀይር መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ግብርናን ከተለምዷዊ አሰራር አላቆ ወደ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ለማሸጋገር ያለመ አዲስ ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት ውይይት ተደርጎበታል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ይህ ረቂቅ አዋጅ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች ተሰባስበው የራሳቸውን የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ እንዲመሰርቱ የሚያስችል ነው።
ይህም አርሶ አደሩ ምርት አምራች ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱን የሚያቀነባብር የፋብሪካ ባለቤትና መካከለኛ አልሚ እንዲሆን በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰብሳቢው አክለውም፣ አዋጁ አርሶ አደሩ መሬቱን፣ እንስሳቱንና ጉልበቱን ወደ ካፒታል በመለወጥ ከደላላ ብዝበዛ ነፃ ሆኖ በቀጥታ የገበያ ተጠቃሚ እንዲሆን ያግዘዋል ብለዋል።
በአስረጅነት በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ፤ ቋሚ ኮሚቴው በአዋጁ አወቃቀርና በስራ አመራር ቦርድ ዙሪያ ያነሳቸውን የማሻሻያ ሃሳቦች በመቀበል ቀጣይ እርማቶች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል፣ ረቂቅ አዋጁ ላይ “አነስተኛ ይዞታ” ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጓሜ የክልሎችን ተጨባጭ የመሬት አወቃቀር ታሳቢ እንዲያደርግና በኩባንያዎቹ የአመራር ቦርድ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ በፍትሃዊ ውክልና እንዲቀመጥ በቋሚ ኮሚቴው በኩል ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የግብርና ሚኒስቴር የህግ ስራ አስፈጻሚ አቶ በለጠ ሰይፉ በበኩላቸው፤ አዋጁ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተተ በመሆኑ፣ በገጠር የሚገኘውን ማህበረሰብ ህይወት በዘላቂነት ለመቀየርና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ፣ ግብርናውን ከኑሮ መደጎሚያነት ወደ ትርፋማ የንግድ ዘርፍ በማሸጋገር የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ልዑል ወልዴ
ሰኔ 03/2018 ዓ.ም
