በኢትዮጵያ አደጋዎች ሲከሰቱ የመደበቅና መረጃዎችን በአግባቡ የመመዝገብ ችግር እንዳለ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ አደጋዎች ሲከሰቱ የመደበቅና መረጃዎችን በአግባቡ የመመዝገብ ችግር እንዳለ የተገለጸው በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ጤናና ደህንነት ኮንፈረንስ ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤና አጠባበቅን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመው ይህ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር ከጄኔቫው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ዋስትና ማህበር (ISSA) ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ፣ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችና መፍትሄዎቻቸው በስፋት ተመክሮባቸዋል፤ በዘርፉ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ሶፎንያስ ደነቀ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን መድረክ በማዘጋጀት ከአፍሪካ ሶስተኛዋ ሀገር መሆን ችላለች ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ ያለው የኮንስትራክሽን እድገት ፈጣን ቢሆንም፣ ከደህንነትና ጤና አጠባበቅ አንጻር ግን አሁንም በጅማሮ ደረጃ ላይ መሆናችንን ጠቁመዋል።
ኢንጅነር ሶፎንያስ “ቪዥን ዜሮ” (Vision Zero) የተሰኘውን ዓለም አቀፍ መርህ በማንሳት፣ ይህ መርህ በግንባታ ሂደት ላይ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይከሰት የማድረግ ግብ ያለው ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን አደጋዎች ሲከሰቱ የመደበቅና መረጃዎችን በአግባቡ የመመዝገብ ችግር እንዳለ ገልጸዋል።
ይህንን ለመቅረፍም “ኒር ሚስ” (Near miss) የሚባሉ፣ ለጥቂት የተረፉ አደጋዎችን ጭምር መዝግቦ የሚይዝ የቴክኖሎጂ ሥርዓትና ዳታቤዝ ለመፍጠር ማህበሩ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዘርፉ የሚታየውን ትልቁን ተግዳሮት ሲያስረዱም፣ “የኮንስትራክሽን ደህንነት እንደ ቅንጦት እና እንደ ተጨማሪ ወጪ የሚታይበት የተሳሳተ አመለካከት ሊቀየር ይገባል” ብለዋል። ግንባታዎች ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ፍጻሜያቸው ድረስ ለባለሙያዎችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ደህንነት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው፣ ለዚህም የባለሀብቶች፣ የኮንትራክተሮችና የሱፐርቫይዘሮች በጋራ ተጠያቂነት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኮንፈረንሱ የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ከጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኦስትሪያና ናይጄሪያ የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
አዲስ አለም አበበ
ሰኔ 08/2018 ዓ.ም
