በደቡብ ምስራቅ እስያ በህገ-ወጥ ደላሎች ተታለው የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት በተለይም በሚያንማር፣ በካምቦዲያና በላኦስ ችግር ውስጥ የነበሩ ከ1 ሺህ 3መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ የተሰኘው ድርጅት አስታወቀ።

ተመላሾቹ በህገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት “ከፍተኛ ክፍያ ያለው ስራ አለ” በሚል ተታለው ወደ ታይላንድ ከተጓዙ በኋላ፣ በግዳጅ ድንበር ተሻግረው በሚያንማር በሚገኙ የኢንተርኔት ማጭበርበሪያ ማዕከላት ውስጥ ታስረው እንዲሰሩ ይገደዱ እንደነበር ተገልጿል።

ንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ እንደገለጸው፥ እነዚህ ዜጎች በታጠቁ አካላት እየተጠበቁ ለወራት በሰው መብት ረገጣና በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ቆይተዋል።

ድርጅቱ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ዜጎቹን የማስመለስና የመልሶ ማቋቋም ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል።

ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ዜጎች የተጎዳ የስነ-ልቦና ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መለኪያ መሰረት አብዛኞቹ ከተገቢው የአዕምሮ ጤና ደረጃ በታች መሆናቸው በጥናት መረጋገጡ ተጠቁሟል።

ህብረተሰቡ በተለይም የተማሩ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎች እንዳይታለሉ ድርጅቱ አሳስቧል።

ሊዲያ ደሳለኝ

ሰኔ 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *