ትራምፕ ከአርብ በፊት የአሜሪካ-ኢራንን ስምምነት ይፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ቫንስ ገለጹ


የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ያለውን ጦርነት ለማቆም የተደረሰውን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ከአርብ በፊት ይፋ ለማድረግ ሊወስኑ እንደሚችሉ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ገለጹ። ይህ የተባለው ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱ አስቀድሞ መፈረሙን ከተናገሩ በኋላ ነው።
 
ቫንስ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት (MOU) “አንድ ገፅ ከግማሽ ገደማ” የሚሆን እና “በጣም አጠቃላይ” ይዘት ያለው ሰነድ ሲሉ ገልጸውታል።
 
ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናትም ስለ ስምምነቱ አንዳንድ ዝርዝር መረጃዎችን መስጠት የጀመሩ ሲሆን፥ ስምምነቱ በጄኔቫ በይፋ በሚፈረምበት አርብ እለት የሆርሙዝ ወሽመጥ  ዳግም ክፍት እንደሚሆን ገልጸዋል።
 
ይህ የተሰማው ትራምፕ በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የ G7 ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ባሉበት ወቅት ሲሆን፥ ጉባኤው ዛሬ ማክሰኞ  የግብፅ፣ የኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መሪዎች የሚታደሙበት ስለ ኢራን ጉዳይ የሚያጠና ልዩ የውይይት መድረክ ያስተናግዳል።
 
በትላንት ሰኞው  ትራምፕ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይት፥ ስለ መጀመሪያው ደረጃ ስምምነት ሲናገሩ “ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ መፈረሙን ለመናገር በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።
 
የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደገለጹት  ስምምነቱ በራሳቸው በትራምፕ፣ በቫንስ እና በኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ መሀመድ ባገር ጋሊባፍ በዲጂታል መንገድ ተፈርሟል።
 
የባለስልጣናቱ መግለጫ አክሎ እንደሚያመለክተው በኢራን የኒውክሌር መርሃ-ግብር ዙሪያ የሚደረጉ የቴክኒክ ውይይቶች በዚህ ሳምንት ይጀምራሉ ተብሎ የሚጠበቅ  ሲሆን፥ ማናቸውም የኢኮኖሚ ማዕቀቦች መነሳትም ሆነ የታገዱ ሀብቶች መልቀቅ የሚወሰነው ኢራን በስምምነቱ ውስጥ የገባቸውን ግዴታዎች በመወጣቷ ላይ ይሆናል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
 
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *