በአነጋጋሪ ድርጊቶቻቸው የሚታወቁት ኢታማር ቤን-ጊቪር፣ ለባዮሜትሪክ የጣት አሻራ በአካል እንዲቀርቡ ከተጠየቁ በኋላ የቤተሰብ ጉብኝታቸውን እንደሰረዙ ተዘግቧል።
የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር ቪዛ በማግኘት ረገድ በገጠማቸው ችግር ምክንያት ወደ አሜሪካ ለማድረግ አቅደውት የነበረውን የቤተሰብ ጉዞ መሰረዛቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ቤን-ጊቪር ለቪዛው ሂደት አካል የጣት አሻራ ለመስጠት በአካል መቅረብ እንዳለባቸው እንደነገራቸው ‹‹ሀሬትዝ›› የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ይህ መስፈርት በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ቪዛውን ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆን እንደመጣ ተደርጎ ተተርጉሟል።
ሚኒስትሩ በማያሚ በሚካሄድ የአንድ እስራኤላዊ ነጋዴ ሴት ልጅ ሰርግ ላይ ለመታደም ሊጓዙ እንደነበር ተገልጿል።
ቤን-ጊቪር መጀመሪያ ላይ ነጋዴው የጉዞ ወጪውን እንዲሸፍንላቸው ጠይቀው እንደነበር ነገር ግን ከሀገሪቱ ዋና ተቆጣጣሪ የመጣውን ትችት ተከትሎ ወጪውን ራሳቸው ለመሸፈን ተስማምተው እንደነበር ‹‹ሀሬትዝ›› ቀደም ብሎ ዘግቧል።
ቤን-ጊቪር በሰፊው ትችት እና ዓለም አቀፍ ውግዘት በሚያስከትሉ ቀስቃሽ ድርጊቶቻቸው በተደጋጋሚ በዜናዎች ላይ የሚነሱ ግለሰብ ናቸው።
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም
