ለሶስት ዓመታት ለብቻዉ ጥቅጥቅ ባለ ደን ዉስጥ ከሁሉም ነገር ተለይቶ የኖረዉ ጎልማሳ

ባለፈው ሳምንት የኢንዶኔዢያ መገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ሱካቡሚ ግዛት በሚገኘው የሳላክ ተራራ ጥቅጥቅ ያለ ደን ዉስጥ የተከናወነ አንድ ልብ አንጠልጣይ ታሪክ ይዘው ወጥተዋል።

ታሪኩ በጥቅጥቅ ሕይወት አልባ በሆነው ጫካ ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል ተለይቶ የኖረውን የ49 ዓመቱን ጎልማሳ ተዓምራዊ መትረፍ የሚያወሳ ነው።

ከባድ ዝናብ ከጣለ በኋላ የወንዙን ፍሰት ለመታዘብ የወጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የአልጌ ወይንም አረንጓዴ ምንጣፍ በለበሰ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ፣ ሙሉ በሙሉ ዝናብና ንፋስ ያደቀቀው፣ ግራ የተጋባና የፈዘዘ ሰው አገኙ።

አስገራሚውን የነፍስ አድን ሥራ ያከናወኑት ነዋሪዎች እንደገለጹት፥ ሰውየው የመናገር አቅሙ ተሟጦ ነበር።

የአካል ቁመናውም ቢሆን ከአጥንትና ቆዳ በቀር ምንም አልቀረውም፤ በራሱ መቆም ቀርቶ መራመድ እንኳ ተስኖት ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ሰዎችን ሲያይ ፍርሃትና ድንጋጤ ይነበብበት ነበር።

ወዲያውኑ ተሸክመው ከጫካው ካወጡት በኋላ፥ በዘመናዊ የጣት አሻራ እና በአይን ብሌን ቅኝት ማንነቱ እንዲለይ ወደ አካባቢው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ወሰዱት።

ያ የተገኘው ምስኪን ሰው የ49 ዓመቱ አይ ሶሌሁዲን መሆኑ ተረጋገጠ።

የግዛቱ ነዋሪ የነበረው አይ፥ ከሦስት ዓመታት በፊት በቤተሰቦቹ መጥፋቱ ተመዝግቦ የነበረ ሰው ነው። ወደ ስፍራው የመጡት ቤተሰቦቹም ልጃቸውን ወዲያውኑ አውቀውታል።

እንደ ቤተሰቦቹ ገለጻ፥ አይ ከባድ የአዕምሮ ጤና እክል ነበረበት፤ በአንድ እኩለ ቀን ወደ ሳላክ ተራራ ደን ካመራ በኋላ ግን ጭራሽ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

ቤተሰቦቹ በመንደሩ ዙሪያ ባለው ሰፊ ጫካ ውስጥ ተስፋ ሳይቆርጡ በተደጋጋሚ ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም።

ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ ጊዜ በተዓምር ነፍሱን ጠብቆ መቆየት ችሏል።

አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች ስለመታየቱ ጥቆማዎች ይደርሱ የነበረ ቢሆንም፥ ቤተሰቦቹ ፍለጋ ቦታው ድረስ ከመድረሳቸው በፊት መልሶ ወደ ጥቅጥቅ ጫካው ውስጥ በመግባት ይሰወር ነበር።

አይ ሶሌሁዲን በዚህ በሳላክ ተራራ አስፈሪ ጫካ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንዳሳለፈ በትክክል ባይታወቅም፥ የደረሰበት ከፍተኛ የአካል መክሳት፣ መድከምና የሰውነት ፈሳሽ መሟጠጥ ግን ያለ በቂ ምግብና መጠለያ ለረጅም ጊዜ ለብቻው ተንከራቶ እንደነበር ይመሰክራል ተብሏል፡፡

የአይ ወንድምና እህቶች በሐዘንና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆነው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ አይ የአዕምሮ መታወክ ምልክት ማሳየት የጀመረው ወላጆቻቸው ካረፉ በኋላ ነበር።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብቻውን ወደ ጫካ የመንከራተትና የመጥፋት ልማድ ነበረው። በመጨረሻ ግን ያ ልማዱ ለሦስት ዓመታት ሙሉ ከቤተሰቡ ነጥሎት ቆይቶ፥ እነሆ ዛሬ በፈጣሪ ተአምር በሕይወትተመልሷል።

ሀና ሰይፉ

ሰኔ 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *