ቫንስ በበኩላቸው በባሕረ ሰላጤው ሀገራት የሚመራ የ300 ቢሊየን ዶላር ፈንድ መኖሩን ጠቆሙ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አሜሪካ ክፍያ ትፈጽማለች የሚሉ ዘገባዎችን ‹‹ሀሰተኛ ዜና››ሲሉ አጣጥለዋል፤ባለስልጣናት ደግሞ ለመልሶ ግንባታ የሚውለው ካፒታል ከግል ባለሀብቶች የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን ለኢራን የገንዘብ ክፍያ እየፈጸመች ነው የሚለውን ወሬ ውድቅ አድርገዋል።
ስለ ብዙ ቢሊየን ዶላር የመልሶ ግንባታ ፓኬጅ በሚወሩ ዘገባዎች መካከል የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ አለ መባሉን ‹‹ሀሰተኛ ዜና›› ሲሉ ጠርተውታል።
ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ‹‹አሜሪካ ለኢራን 300 ሚሊየን ዶላር እየከፈለች ነው የሚለው ወሬ ሀሰተኛ ዜና ነው›› ሲሉ አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እንደገለጹት፤ ማንኛውም የታቀደ የ3መቶ ቢሊየን ዶላር ፈንድ የሚገኘው ከአሜሪካ ግብር ከፋዮች ሳይሆን ከቀጣናው አጋሮች ነው።
ቫንስ ለኤንቢሲ ኒውስ ሲናገሩ ‹‹ከዚያ ገንዘብ ውስጥ አንዲት ሳንቲም እንኳ ከአሜሪካ የሚወጣ የለም›› ብለዋል።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ቀደም ብለው እንደተናገሩት፤የብዙ ቢሊየን ዶላር ፈንድ የዲፕሎማሲያዊ ውይይቶቹ አካል ቢሆንም ማንኛውም የፋይናንስ እንቅስቃሴ ግን በጥብቅ ‹‹ከአፈጻጸም››ጋር የተያያዘ ነው።
ፋይናንሻል ታይምስ እንደጠቆመው፤ ካፒታሉ የሚተዳደረው ከመንግስት ወደ መንግስት በሚደረግ ቀጥተኛ እርዳታ ሳይሆን በኢራን ገበያ ላይ ፍላጎት ላላቸው የግል ኩባንያዎች በሚዘጋጅ መዋቅር አማካኝነት ሊሆን እንደሚችል ዘገባው አመልክቷል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም
