የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ በመሆን በኢኮ ኢንደስትሪያል ፓርክ ውስጥ ያስገነቡትን አራተኛውን የኢቪ (EV) ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪናዎች ማደያ ጣቢያ ዛሬ በይፋ አስመርቀዋል።
በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሁለቱ ስትራቴጂካዊ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት የሥራ አመራሮች ተገኝተዋል።
ይህ አዲስ ጣቢያ ሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር እና ከቅሪተ-አካል ነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ የጀመረችውን የትራንስፖርት ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ የሚገኙ ሲሆን፣ ፍላጎታቸውን ለማሟላትም በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ከ15 በላይ ፈጣን የኢቪ ቻርጀሮች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በተጨማሪም ከ80 በላይ በሚሆኑ ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማትን ተከትሎ የማስፋፋት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ይህም ሀገሪቱ ያስቀመጠችውን የዜሮ ካርቦን ልቀት (Zero Emission) ግብ ለማሳካት እና አካባቢን የማይበክል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ አጋዥ እንደሚሆን ተገልጿል።
ዛሬ ወደ ሥራ የገባው ዘመናዊ የኃይል ማደያ ጣቢያ በአንድ ጊዜ 24 መኪኖችን በከፍተኛ ፍጥነት የማገልገል አቅም አለው።
በተለይም ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ በሌለበት የሌሊት ክፍለ-ጊዜ መኪኖችን ቻርጅ በማድረግ ደንበኞች በቅናሽ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር የተዘረጋለት በመሆኑ፣ ለትራንስፖርት ዘርፉ ዕድገትና ለተጠቃሚዎች ትልቅ እፎይታን ያመጣል ተብሎ ይታመናል።
ለዓለም አሰፋ
ሰኔ 10/2018 ዓ.ም
