‹‹የሰልጣኞች ቁጥር አናሳ ነው የሚለው መረጃ የተዛባ ነው››- የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት

ወደ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሚመጣው የሰልጣኝ ቁጥር አናሳ ነው በሚል የሚሰራጩ መረጃዎች ፍጹም የተዛቡ መሆናቸውን የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ዘርፉን አስመልክቶ የሚናፈሱት መረጃዎች እውነተኛውን ተጨባጭ ሁኔታ የማይወክሉና የተዛቡ ናቸው ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በየዓመቱ የሚመዘገበው የሰልጣኞች ቁጥር ከስድስት ሚሊየን በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ቁጥር በመደበኛና በአጫጭር ሥልጠናዎች የሚመዘገቡትን ያጠቃለለ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ብሩክ፤ ወደ ዘርፉ የሚመጣው የላቀ ፍላጎት ያለው ወጣት ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ሆኖም ግን ወደ ቴክኒክና ሙያ መምጣት ከሚገባውና አገሪቱ ከምትፈልገው አጠቃላይ የሰው ኃይል አንጻር ሲታይ ገና ብዙ መሰራት እንደሚቀረውና ማህበረሰቡ ለሙያ ያለው ግንዛቤ ሊያድግ እንደሚገባም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የሀገራት የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ጥንካሬና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በሀገር ውስጥ በሚፈልቁ የፈጠራ ስራዎችና በሰለጠነ የሰው ኃይል መሆኑም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑም በቆይታችን አንስተዋል።

ልዑል ወልዴ

ሰኔ 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *