የሲቢኤስ ኒውስ የሕዝብ አስተያየት ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ አሜሪካውያን ከኢራን ጋር ያለው ግጭት እንዲያበቃ የሚደግፉ ሲሆን፤ ዩናይትድ ስቴትስ የቴህራንን የኑክሌር መርሃ ግብር በቋሚነት ማቆሟ ላይ ግን ጥርጣሬ አለ ይላል።
በቅርቡ በአሜሪካ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው 37 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን የተደረሰው ስምምነት ለኢራን ያደላ እንደሆነ ያምናሉ።
ሲቢኤስ ኒውስ እና ዩጎቭ 2 ሺህ5መቶ19 አሜሪካውያንን በማሳተፍ ከኢራን ጋር ስለተደረገው ስምምነት ጥናት አካሂደዋል።
በጥናቱ መሠረት 37 በመቶ የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች ስምምነቱ ‹‹ለኢራን የተሻለ›› ነው ሲሉ፤ 22 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ‹‹ለአሜሪካ የተሻለ›› ነው ብለዋል።
78 በመቶ ያህሉ ምላሽ ሰጪዎች በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን መካከል ያለው ግጭት እንዲያበቃ እንደሚደግፉ ሲገልጹ፤ 22 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ‹‹ኢራን እጅ እስክትሰጥ ድረስ›› ግጭቱ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን የኑክሌር መርሃ ግብር በቋሚነት አቁማለች ወይ በሚለው ጥያቄ ላይ 31 በመቶ የሚሆኑት ‹‹አዎ›› ሲሉ፤ 69 በመቶ የሚሆኑት ግን ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ 36 በመቶ የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ያለውን ሁኔታ በያዙበት መንገድ ሲስማሙ፤ 64 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ተቃውመዋል።
ሀና ሰይፉ
ሰኔ 15/2018 ዓ.ም
