በመዲናዋ “የመሬት ባንክ” መደራጀት የህገ-ወጥ ወረራን እንዲቀንስ ማድረጉ ገለጠ

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት መረጃ በዲጂታል የመሬት ባንክ መደራጀቱ፣ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉን የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ።
 
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ፣ ወደ መሬት ባንክ በገቡ ይዞታዎች ላይ “ምንም አይነት” ህገ-ወጥ ወረራ አልተፈጸመም ብሏል።
 
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የምስራች ግርማ  ለኢትዮ ኤፍኤም 107.8 እንደገለጹት፤ ተቋማቸው ከመሬት ልማትና ማስተዳደር ቢሮ ጋር በመቀናጀት ወደ መሬት ባንክ የገቡ ይዞታዎችን በንቃት የመጠበቅና የመቆጣጠር ስራ እየሰራ ይገኛል።
 
ይህ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረገው በይፋ ተለይተው፣ በካሬ ሜትር ተሰልተውና ሙሉ መረጃቸው በዲጂታል የመረጃ ቋት ውስጥ በገቡ የመንግሥት መሬቶች ላይ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ አሰራሩ የገበሬ ወይም የግለሰብ ይዞታዎችን እንደማይጨምር አስገንዝበዋል።
 
አቶ የምስራች አክለውም፤ አንድ መሬት ወደ መሬት ባንክ ሲገባ ይፋዊ መለያ ታፔላ የሚለጠፍበት መሆኑን ገልጸው፣ አልፎ አልፎ በሌሊት የሚደረጉ ህገ-ወጥ የአጥር ማጠርና የመስፋፋት ሙከራዎች ቢኖሩም፣ በቦታው በተመደቡ ኦፊሰሮች አማካኝነት ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድ መሬቶቹን ንፁህ አድርጎ ማቆየት መቻሉን ጠቁመዋል።
 
የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በሚፈልግበት ጊዜም፣ የቦታው ዝርዝር ሁኔታና የካሬ ሜትር መጠኑ ተጠቅሶ በደብዳቤ ሲጠየቅ ወዲያውኑ ለልማት ተላልፎ እንደሚሰጥ ተነግሯል።
 
ከዚህ ቀደም መሬቶች በይፋ ሳይለዩና መረጃቸው ሳይደራጅ በመቆየቱ ምክንያት ቁጥጥሩ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን መሬቶቹ በካሬ ሜትር ተለይተው በባንክ መያዛቸው ቁጥጥሩን ግልጽና ምቹ እንዳደረገው ተገልጿል።
 
እድላዊት ብርሃኑ

ሰኔ 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *