ህገ-ወጥ ስደተኞችን ለመቃወም ሰኔ 30 በታቀደው ሰልፍ ምክንያት መንግስት ጥብቅ የጸጥታ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ ዜጎች የህግ የበላይነትን እንዲያከብሩ እና እንዲረጋጉ አሳስቧል።
‹‹ማርች ኤንድ ማርች›› በተባለው ቡድን የተደራጀው ይህ ሰልፍ ህገ-ወጥ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ከተቀመጠው ቀነ-ገደብ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ ነው።
የሰልፉ አስተባባሪዎች ዓላማቸው ጥብቅ የስደተኞች ህግ እንዲተገበር መጠየቅ ብቻ እንደሆነና ሰልፉ ሰላማዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።
መንግስት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ግን የተጠቀሙበት ንግግር በስደተኞች ላይ ፍርሃትንና መፈናቀልን እየፈጠረ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጋውቴንግ፣ ክዋዙሉ-ናታል፣ ዌስተርን ኬፕ እና ኢስተርን ኬፕ ግጭት ሊነሳባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ተብለው ተለይተዋል።
የአገሪቱ ፖሊስ ማንኛውም በሀገሪቱ ውስጥ ያለ ሰው ህጋዊም ሆነ ህገ-ወጥ የሕገ-መንግስት ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው ገልጾ፣ በራስ ፍቃድ እርምጃ መውሰድ ወይም ጥቃት መፈጸም በፍጹም እንደማይቻል አስታውቀዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ1መቶ60 በላይ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
በተጨማሪም ማላዊ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ ዜጎቻቸውን በፈቃደኝነት ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ መንግስትም ሂደቱን ለማፋጠን ጊዜያዊ የመመለሻ ማዕከላትን አቋቁሟል።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ይህ በስደተኞች ላይ የሚታየው ጥላቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የሀብት እጥረት እና የኢኮኖሚ ውድድር ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ሳራ ዮሐንስ
ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
