በአርሲ ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የምክር ቤት ውሎአቸው፤ ሁኔታውን በሶሻል ሚዲያ ሲያባብሱ በነበሩ አካላት ላይም ጥብቅ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ በአርሲው ግጭት ዙሪያ የተወሰዱ የሕግ ማስከበር እርምጃዎችን በዝርዝር አቅርበዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በግጭቱ እጃቸው ያለበት 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን፣ ግጭቱን ለማባባስና በሐሰተኛ መረጃዎች ሁኔታውን ወደ ሃይማኖታዊ ግጭት ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላትም ተለይተው በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋል ጀምረዋል።
በአካባቢው የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአሁኑ ወቅት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀሪዎቹንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም የመንግሥት የሕግ ማስከበርና የመልሶ ማቋቋም እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።
በግጭቱ ወቅት 11 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የጠቀሱት ዶክተር ዐቢይ፣ ከነዚህም ውስጥ ስምንቱ ሕዝባቸውን ከአጥፊዎች ለመከላከል ሲፋለሙ የወደቁ የፖሊስና የሚሊሻ አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ጉዳዩን የሃይማኖት መልክ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት፣ ንጹሃንን ለመታደግ መስዋዕትነት የከፈሉ የጸጥታ አካላትን ክብር የሚነካና ተገቢ ያልሆነ ተግባር መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ በሶሻል ሚዲያ አማካኝነት የዜጎችን ደም ለፖለቲካ ትርፍ የሚጠቀሙና “የግሩፕ ጨዋታ” የሚጫወቱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና መንግሥት እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በአርሲው ግጭት ወቅት ንጹሃንን ለመታደግ ሲሉ መሥዋዕትነት ለከፈሉ የጸጥታ አካላት ምክር ቤቱ የክብር ምስጋና እንዲያቀርብ በጠየቁት መሠረት፣ የምክር ቤት አባላት በታላቅ ጭብጨባ አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
ልዑል ወልዴ
ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
