የብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን ያሉት በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የተጠናቀቀውን የ2018 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ ባደረጉት ንግግር “የዘንድሮው ምርጫ ለየትኛውም የፖለቲካ አካል እጅግ አስተማሪና የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥልቅ አሳቢነትና ሰላም ወዳድነት በትልቁ ያሳየ ታሪካዊ ሁነት ሆኖ ተመዝግቧል” ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የፊታችን ሐምሌ 8 ቀን መጀመር እንደሚካሄድ መጠቆሙን ተከትሎ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ለኮሚሽኑ ያላቸውን ሥጋትና አስተያየት አቅርበዋል።
ዶክተር ደሳለኝ ኮሚሽኑ ገና በርካታ ተጨማሪ ሥራዎች የሚቀሩት መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የታጠቁ ኃይሎች ትጥቃቸውን ባልፈቱበት ማግስት ይህ ሀገራዊ ጉባዔ መካሄዱ ከፍተኛ ገንዘብና ጊዜ የወጣበት ተቋም ዕቅዱ እንዳይሰናከልበት ያሰጋል ብለዋል። ለዚህም ቀደም ሲል የነበሩትን የዕርቀ ሰላም እንዲሁም የማንነትና ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽኖችን ተሞክሮ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
አክለውም ሀገራዊ ምክክሩ ሲካሄድ ተቋሙ ከመንግሥት ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሚሆንበት አሠራር ሊዘረጋ እንደሚገባና በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የችኮላ አካሄድ መቅረፍ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ የአንድ ፓርቲ የሥልጣን ዘመን ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳይሆን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ማቅረቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ
